Discussion Forum

 የትምክህተኝነትና የጠባብ ብሔርተኝነት አደገኛነት ገላውዴዎስ አርአያ ዶ/ር

by Tigrayonline.

ሰሞኑን አንድ ጓደኛዬ ካመላከተኝ በኋላ ወደ አሲምባ ድረገጽ ጎራ ብዬ ነበር። ይኸንን ድረገጽ ቁምነገር አዘል ወይም ለኢትዮጵያ የሚበጅ ርእሰነገሮችና በጥናትና ምርምር የተመረኮዘ ጥናቶችን ስለማይለጥፍ እንኳንስ ልጎበኘው መኖሩንም አላስታውሰውም። አሁንም ቢሆን ድረገጹን የዳሰስኩት ከላይ የተጠቀሰውን ወዳጄ “ስላንተ የተጻፈ አለ ግን ዘለፋ ብቻ ነው፥ ዋጋ የለውም” ብሎ አስተያየቱን በስልክ ከነገረኝ በኋላ፥ እኔም እስቲ ልመልከተው፥ ምን ጽፈው ይሆን በማለት ድረገጹን ከፈትኩት። አርእስቱ የትግራይ ምሁራን ቀጣይ ዝቅጠት ለምን? (ይድረሰ ለገላውዲዮሰ አርአያና ተኮላ ሐጎሰ) የሚል ሆኖ ደራሲው ደግሞ አደመ በላቸው ይባላል። በዚሁ ምላሽ ጽሑፍ እኔን በሚመለከት ብቻ ነው የማቀርበው፥ ለመንደርደርያ ያህል ግን አሲምባ ድረገጽና አዘጋጆቹ የሚያቀርቧቸውን ተባራሪ ጽሑፎችን አስመልክቶ አስተያየት መሰንዘር እፈልጋለሁ። ድረገጹ “ኢሕአፓ እኛ ብቻ ነን” በሚሉ ትምክህተኞችና አሁን ወደ ጠባብ ብሔርተኝነት ያዘቀጡ ግለሰቦች የሚዘጋጅ ሆኖ እስካሁን ድረስ አንዳችም ትምህርታዊና ገንቢ ጽሑፍ አቅርበው አያውቁም። ሰለሆነም ድረገጹና አዘጋጆቹ በኔ ላይ ያደረጉት ውርጅብኝ የሚያስደንቅ አይሆንም፥ ባሉቧልታና በውሸት የተካኑ ነውና ምሁራዊ ጽሑፍ እንድያቀርቡ አይጠበቅባቸውም። ለነገሩ፥ ብቃትም የላቸውም። እኔ በበኩሌ ቅር አልሰኝም፥ አልከፋኝም። እንዲህ ዓይነቶቹ የስነልቦና አካለ ስንኩላን ከሕብረተሰባችን አብራክ ለመውጣታቸው ግን ለሃገሬ ለኢትዮጵያ አዝንላታለሁ። እኝህ ትምክህተኞችና ጠባብ ብሔርተኞች ከየት የፈለቁ ናቸው? በሽታው የተጠናወተባቸው ደግሞ ከመቸ ወዲሀ ነው? ድሮ በኢትዮጵያ ተማሪዎች ንቅናቄና ኋላም በኢሕአፓ ተራማጅ ሃይሎችና አብዮታውያን ያራመዱት ርእዮተዓለምና የፖለቲካ መስመር መላ ኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን ዓለምአቀፋዊ ባሕረሓሳብም ጭምር ያካተተ ነበር። የዚሁ ትውልድ ታጋዮች አብዛኞቹ የደርግ የቀይ ሽብር ሰለባ ከመሆናቸው ባሻገር በትግል አውድማ የወደቁም አሉ። ለዚሁ ትወልድ፥ በተለይም ለተሰዉ ጓዶች ከፍተኛ ክብር ነው ያለኝ። ነገር ግን ጓዶቹ በርእዮተዓለምና ፖለቲካዊ ምህዳር አመርቂ ክንውኖች ቢያደርጉም ቅሉ እንዳሰቡትና እንዳቀዱት ግባቸውን በግብር መተርጎም አልቻሉም። እንኳንስ ድል ሊቀዳጁ ይቅርና እትብታቸው በተቀበረበት ዘየ መኖር አልቻሉም፤ከሃገራቸው ውጭ ተሰደው እንዲኖሩም ተገደዋል። ይህ ችግር የተከሰተው ግን ከድክመታቸው ብቻ ሳይሆን የታሪክ አጠቃላይ አቅጣጫ አመቺ ሁኔታ ባለመፍጠሩና የሃገርና የዓለምአቀፍ ተጽእኖዎችም ስለተጨመሩበት ነው። አሁን አቶ አደመ በላቸው እና የአሲምባ ድረገጽ አዘጋጆች የድሮ የኢትዮጽያውያን ተራማጅ ሃይሎች ያነገቡትን ዓለምዓቀፋዊ ርእዮተዓለም እርግፍ አድርገው በመተው የትምክህትና ጠባብ ብሔርተኝነት ጣምራ ፖለቲካ እያራመዱ ይገኛሉ። ድሮ የኢትዮጵያ ተማሪዎች ንቅናቄ ትምክህተኛነት የሚመነጨው ወይም የሚንጸባረቀው በመደብ ገዢዎችና አጋሮቻቸው ወይም የዚሁ መደብ አፈቀላጤዎችና ጋሻዣግሬዎች ከሚያራምዱት የአቆርቛዥና 2 2 ምዝበራ የባሕረሐሳባዊ ጫና ነበር በማለት ርትዓዊ ትንታኔና ገለጻዎች ያደርጉ ነበር። በአንጻሩ ከተገዢ መደብ ሆኖው የጎሳ ፖለቲካ ለሚያራምዱ ሁሉ ጠባብ ብሔርተኞች ይባሉ ነበር። ሁለቱ የርእዮተዓለም ክስተቶች ለኢትዮጵያ አንድነት አደጋ ከማስከተላቸው በላይ ሃገርን የሚበትን አጀንዳ ነው የሚያራምዱትና የሚያበረታቱት። አሁን የሚገርመው ግን፥ በትግርኛ “ዘመነ ግሪንቢጥ ማይ ንዓቐብ” (በተገላቢጦሽ ዘመን ውሃ የሽቅብ ይፈሳል) እንደሚባለው ሁሉ የተራማጅነት መፈክር አንግቦ ይንቀሳቀስና ይዘምር የነበረውን የሁለቱ አደጋዎች ዋና አስተናጋጅ ሆኖ መገኘቱ ነው። ይብላኝ ለወደቀው ኢትዮጵያዊ ጀግናና አርበኛ የሚያሰኝ ነው። ከፍ ብየ እንደጠቀስኩት የዚሁ ጣምራ አደጋዎች አሁን በነ አደመ በላቸው እና መሰሎቻቸው የሚተገበር ሆኖ ምን ያህል እንዳዘቀጡና እንደከሰሩ ከበራሪ ጽሑፎቻቸው በቀላሉ መረዳት ስለሚቻል አንባቢ በይበልጥ ግንዛቤ ይኖሮው ዘንድ አደመ በኔ ላይ የሰነዘረው መሰረተቢስ “ነቀፌታ” እንደሚከተለው አቅርቤዋለሁ፦ “ጸረ አማራው ጸረ ምኒሊኩ ገላውዲዎስ ማነው? ሩቅ ሳንሄድ የትግራይ ተወላጅ ነው፥ ያኔ አብዮት ትግል ሲባል - እሱ ብቻ ሳይሆን ሌሎችንም - ወስዶ ኢሕአፓ ውሰጥ ከተታቸው። ከከተማ ወደ አሲምባ ሄዶ ፋኖ ነኝ አለ። ሳይወል ሳያድር ወደ ወሎ ዘመቻ በሚለው በፍርሃትና ሌላም ጉዳት በማስደረስ ተከሶ ከቆየ በኋላ ወደ ሱዳን ተሸኘ። ከሱዳን - እንደ ሌሎቹ - ወደ አመሪካ አቀናና ትምህርቱን ተከታትሎ ዶክተር ተባለ፥ ሌሎች ትግሉን ቀጥለው ከደርግም ከወያኔም ሲዋደቁ እሱ ቤተሰብ መሰረተ፥ ደረጀ፥…ወያኔ ወደ ስልጣን ሊጠጋ ሰሞን ገላውዲዎስ ወየነ። ተገረ ይላሉ ዛሬ ዜጎች…ትግሬነቱ ገነፈለ ማለት ነው ይባላል…ወያኔ ስልጣን እንደያዘ ገላውዲዮሰ ወያኔን የሚያስደስትና የሚጠላውን አማራና ኢሕአፓ የሚያወግዝ መጽሐፍ በእንግሊዝኛ አሳተመ። የወያኔ ኮሜንተተር ዋና አዘጋጅ ሆኖ የወያኔን ፕሮፓጋንዳ አሰራጨ። ወያኔን ማመስገን አይሁንብኝ እንጂ ወያኔ ለአድርባዮች መድሃኒትም መርዝም ነው፥ ሊሰግዱለት ያሉትን ያባርራል - ቂም አይረሳም፥ አልያም ነገ እኔንም ይክዳሉ ብሎ ወጊድ ይላቸዋል። ለገላውዲዮስም የተለየ መልክ አላሳየውም፥ ወግድ፥ በዝያው በርቁ ነው ያለው።…ገላውዲዮሰ አማራን እንደሚጠላ በብዙ ጽሑፎቹ ግልጽ አድርጓል።…ወያኔ ለኢትዮጵያ የመጣ ዴሞክራሲያዊ መፍትሔ ነው ያለውና ሀገር ወዳድ ሀይሎችን ያወገዘው ማን ነው?ገላውዲዮሰ! ትግራይ የምትኮራባቸው ልጆች አፍርታለች።” ዝባዝንኬውን ሙሉ በምሉ ማንበብ ከፈለጉ የሚከተለውን ዋቢ መስመር ይክፈቱ፡http://www.assimba.org/Articles/Yetgraye_Mehoroch.pdf ይህ አደመ የተባለው ግለሰብ በሐሰትና አሉቧልታ የተካነ ብቻ ሳይሆን የብእር ስም በመጠቀም ደግሞ ኢትዮጵያውያንን ለማደናገር የሚቃጣ ወንጀለኛ ነው። የዛሬ ሰባት ዓመት አውግቸው ብሩ በሚል ስም እና ከኃይለሥላሴ ጉግሳ እስከ ዶክተር ዜሮ፤ ከገላውዲዎሰ አርአያ እስከ ስየ አብርሃ በሚል ርእስ ‘ደብተራው’ በተባለው ድረገጽ እንዲለጠፍ አድርጎ ነበር። ይህ ደንቃራ ጸሐፊ ግን የዘነጋው አንድ ነገር አለ። የፈለገውን የብእር ስሞች ቢጠቀም እንኳ ባሕርዩና (አድሐሪው ጸባዩ) የአማርኛ ዘይቤ አጠቃቀሙ በቀላሉ ያጋልጠዋል፥ በማስተዋል ለሚያነብ ሰው አወናባጁ ግለሰብ አንድ ሰው ለመሆኑ የሚያጠራጥር አይደለም። ከዚህም አልፎ ተርፎ ግለሰቡ ማን እንደሆነ ብቻ ሳይሆን በኢሕአፓ ከፍተኛ አመራር ሐላፊነት እንደነበረውና አሁን አውሮጳ እንደሚኖር የገለጹልኝ ሰዎች አሉ። አሁን የብእር ስሞችን (የሐሞተቢስ የሕቡእ ስሞች) መቀበሉ የግድ ይላል። የኋላ ኋላ ግን የሕቡኡ ግለሰብ ማንነት ማጋለጤ አይቀርም። 3 3 አውግቸውና አደመ አንድም ሁለትም ናቸው ያልኩበት ምክንያት በ2008 እአአ እና በ2015 እአአ የተጻፉትን አሉቧልታዎች ከሞላ ጎደል አንድ ሆነው ስላገኘሁዋቸው ነው። አቶ አውግቸው በ2008 እአአ እንዲህ ብሎ ጽፎ ነበር፦ “ዶክተር ገላውዲዮስ አርአያ ኢሕአፓ ነበሩ ሲባል ብሰማም በዝያን ጊዜ ታሪካቸውን የማውቀው የለኝም። ለምን ድርጅቱን እንደተዉም በበኩሌ የማውቅው የለም። ዶክተር ገላውዲዎስን የማውቃቸው ወያኔ ከሆኑ ጀምሮ ነው። ወያኔን እያዳነቁና ኢሕአፓን እየተቹ የጻፉትንም መጽሐፍ አንብብያለሁ። ዶክተር ገላውዲዮስ የወያኔ መፅሔት የነበረው ኮሜንቴተር አዘጋጅም ሆኖው የወያኔን ፐሮፓጋንዳ ሲያሰራጩ የነበሩ ናቸው…”። ለዚሁ ጽሑፍ “የኢትዮጵያ ጠበቃ እንጂ የአንድ ብሔር አፈቀላጤ አይደለሁም” በሚል ርእስ ምላሽ ሰጥጬበት ነበር፤አንባቢ በዝርዝር ለማንበብና በወቅቱ የተደረጉትን ልውውጦች ለመገንዘብ ከፈለገ ደግሞ በዚሁ ዋቢ ማየት ይችላል፦ www.africanidea.org/Ethiopian_gardian_Ghelawdewos.pdf የአሁኑ የአቶ አደመ ጽሑፍ የተለየ የሚያደርገው ነገር ቢኖር በውሸት ቅንብሩ ብቻ ነው፥ በ2008 እአአ አቶ አውግቸው እኔ ኢሕአፓ ሞኖሬን ሲክድ፥ ሁለተኛው ገጽታው የሆነውን አቶ አደመ ግን ኢሕአፓ መኖሬን አምኖ ግን ተከስሼ እንደነበር ነው የሚቀላውጠው። አቤት! አቤት! ይሰውረነ ከመዓቱ የሚያሰኝ ነው። በድሮ ጊዜ በኢትዮጵያችን አንድ ግለሰብ ዕድሜው ሐምሳ ከደረሰ ወይም ካለፈው አዛውንት ይባልና ዕድሜው ‘ጸሎተ ዕድሜ’ መሆኑን ማሳሰብያ ይሰጠው ነበር። አዛውንቱም የባህሉን በጎ ገጽታዎች በመንከባከብና በማጎልመስ እንደ መልካም ዜጋ ከውሸት፡ ከመጥፎ ድርጊቶችና ወንጀሎች ይቆጠብ ነበር። አውግቸውና አደመ ግን ዕድሜያቸው ወደ ሰባ ተጠግቶ (ወይም አልፎ) ውሸትን እንደ ማጣፈጫና ማዳመቅያ ፈሊጥ አድርገውታል። የአቶ አውግቸው አሉቧልታና የአቶ አደመ ሐሰት ዓይን ያወጣ ውሸት ለመሆኑ ቀጥየ ከማቀርባቸው ቅድመ ተከተሎች ዝርዝር መገንዘብ ይቻላል፦ ውሸት ፩፡ “ጸረ አማራውና ጸረ ሚኒሊኩ ገላውዲዮሰ ማን ነው?” ምላሽ፡እንኳንስ ጸረ አማራ ልሆን፤አመለካከቱም አይጠጋኝም፤ሐሳቡም የለኝም። አመለካከቴ አሁንም ቢሆን መላ አፍሪቃና መላ ኢትዮጵያ ያካተተ ባሕረሐሳብ ነው። ደንቃራው አደመ የስነልቦና አካለስንኩል ስለሆነ ነው እንጂ እንዲህ ያለ ውሸት አይሰነዝርም ነበር። ካፍንጫው በታች ማየት ተሳነው እንጂ ሌላ የዘነጋው ነገር ቢኖር ኢትዮጵያ የብዙ ብሔርና ብሔረሰቦች አገር ሆና ለአያሌ ዘመናት ህዝቡ በተለያዩ መንገዶች (በጋብቻም ጭምር) ሲቆራኝ መቆየቱ ነው። ስለሆነም እኔም አማራነት ሊኖረኝ ይችላል፥አማራውም የትግራይ ደም ቢኖሮው የሚያስደንቅ አይሆንም። አደመ በላቸው የሚያውቀው ነገር የለም፤ ነገር ግን ‘ከባለ ቤቱ ያወቀ ቡዳ ነው’ እንደሚባለው ሁሉ አደመ እውነትም ቡዳ ነው። አደመ “ጸረ ሚኒሊኩ” ያለኝን ግን ውሸት ቢሆንም ቅሉ እንደ ገጸ በረከት ነው ያየሁት። ይኸም ያልኩበት ምክንያት ደግሞ በሁለት ረገድ ነው፦ ሀ) እኔ ጸረ ማንም የኢትዮጵያ ንጉስ የጻፍኩት ወይም የተናገርኩት የለም። በተቃራኒው የዛሬ ዘጠኝ ዓመት ሰለ ዘመናዊ የኢትዮጵያ ነገስታት (ቴዎድሮስ፤ዮሐንሰ፤ምኒሊክ፤ኃይለሥላሴ እና ልጅ ኢያሱ) ጽፌ ነበር። ቡዳው አደመ አላየውም ይሆናል እንጂ በኦክተበር 2006 እአአ በእንግሊዝኛ Emeye Menelik Abba Dagnew: Emperor of Ethiopia በሚል ርእስ ለአንባብያን አቅርቤ ነበር። ለንጉሱ ያለኝ ከበሬታ በጽሑፉ ተጠናቅሮ የቀረበ ሰለሆነ ማንበብና ሐቁን ማረጋገጥ ለሚፈልግ ሁሉ በኔ ድረገጽ በሆኖው www.africanidea.org ማየት ይችላል፤ 4 4 ለማንኛውም ዋቢ መስመሩ www.africanidea.org/Emeye.pdf ነው። በዛን ጊዜ በርካታ አንባቢዎች ለጽሑፉ ያላቸውን አድናቆት ገልጸውልኝ ነበር። እንድያውም አንድ ኢትዮጵያዊ ጽሑፉን ከመውደዳቸው በላይ ከጀነቫ መልእክት በመስደድ አንኮበር ያሰሩትን የሚኒሊክ አዳራሽ (lodge) እንድጎበኝ የክብር ጥሪ አድርገውልኝ ነበር። ውሸት ፪፡ “ሳይውል ሳያድር ወሎ ዘመቻ በሚለው በፍርሃትና ሌላም ጉዳት በማስደረስ ተከሶ ከቆየ በኋላ ወደ ሱዳን ተሸኘ”። ምላሽ፡ የውሸት ድራማ ይሉታል ይሀ ነው። ነገር ግን አደመ የፈለገውን ጥላሸት ለመቀባት ይሞክር እንጂ ሊሳካለት አይችልም፤ ሐሰቱን በመጠኑም ቢሆን አመርቂ በሆነ መንገድ እስካልደገፈው ድረስ! በመጀመርያ ደረጃ እኔ ‘ጉዳት በማድረስ’ የተከሰስኩብት ነገር የለም። ከኔ ጋር የነበሩ ጓዶች በያገሩ፤ ማለትም በሰሜን አመሪካ፡ በአውሮጳ፡በአውስትራልያ፡ እንዲሁም በአገር ቤት በሂወት ሰላሉ ውሸቱ የሚያሳስበኝ አይሆንም፤ ሐቁን ያውቁታልና ነው። ሐቁን እንናገር ከተባለ ግን አንዳንዴ ፍርጥርጥ አድርጎ ማቅረቡ አስፈላጊ ይሆናል፤ ዕድሜ ለአደመና አውግቸው ለመሳሰሉ ከሃድያን ፍጥረቶች! የሆነውን ነገር በመጠኑም ቢሆን ለአንባብያን ማቅረብ እፈልጋለሁ። ከወሎ ወደ ጎንደር ካፈገፈግን በኋላ እኔ በነበርኩባትና በኮሚሳርነት የመራኋትን ኃይል ፳፯ ወደ አሲምባ ስትመለስ አብራን ከሄደችው ኃይል ፲ ግን ጎንደር ውስጥ እንድትቆይ ተደርጓል። ከኢሐአፓ/ሠ ወያኔ ጦርነት በኋላ ደግሞ ኢሕአሠ አሲምባን ለቆ በሽመዛና አድርጎ ወደ ጀብሃ ወይም ተጋድሎ ሓርነት ኤርትራ (ተሓኤ) ወደሚቆጣጠረው የኤርትራ መሬት ዘለቀ። ሠራዊቱ ቅናፍና እንደደረሰ ብረቱን በጊዝያዊ መልክ ለተሐኤ አስረከበ፤ በተጎርባዕ አድርጎም ወደ ተመደበለት ቦታ ወደ ሸምሸምያ ተጓዘ፤ እዛም ለሶስት ወር ያህል ቆየ። በዚሁ ቆይታችን ነበር የኢሕአሠ ኮሚሳር ደብተራው ጸጋየ ሰለ አንጃዎቹ መገደል በይፋ የነገረን። ያልጠበቅኩት መርዶ ስለነበር በጣም አዘንኩ፤ ልቤም ሸፈተ። ስንብትም ጠየቅኩ። ስለሆነም የኢሕአፓ አመራር ሳይሆን የከሰሰኝ፤ እኔ ነኝ የከሰስኳቸው፤ ‘እነ መዝሙር (ይርጋ ተሰማ)፤ ግርሙ (ጌታሁን ሲሳይ)፤ታሪኩ ወዘተ በመግደላችሁ እፋረዳችኋለሁ፤ ታሪከ ይፋረዳችኋል’ ብዬ። ስንብቱን አስመልክቶ ደብተራው አናግሮኝ ነበር። “አሁን ነው መሄድ የምትፈልገው?” ብሎም ጠይቆኝ ነበር። “አይ! ሠራዊቱ ጎንደር ከተሻገረ በኋላ ነው የምሰናበተው” አልኩት። “ጎሽ” አለ፤ ተያይዘንም ወደ ጸለምት አመራን። ዓዲ ሰላም አከባቢ ለትንሽ ጊዜ ከቆየሁ በኋላ ስንብት በጠየቅኩት መሰረት ወልቃይትን አቋርጬ ሱዳን ገባሁ። በመቶዎች የሚቆጠሩ የኢሕአሠ አባላት ተከትለው መጡ። ከሚውዱት ህዝባቸውና ከታገሉለት ዓላማ ሳይወዱ ተለላዩ፤ ጀግኖች ጓዶቻቸውን ግን አልረሱም። ውሸት ፫፡ “ወያኔ ወደ ስልጣን ሊጠጋ ሰሞን ገላውዲዮስ ወየነ። ተገረ ይላሉ ዛሬ ዜጎች… ትግሬነቱ ገነፈለ ማለት ነው ይላሉ ይባላል”። ምላሽ፡አደመ በላቸው እውነትም ወራዳ ነው! እኔን በተናጠል ለማጥላላት የሞከረ መሰለው እንጂ የትግራይን ሕዝብ ነው የዘለፈው፤ ግን የሚያስደንቅ አይደለም። እነ አውግቸውና አደመ፤ ወይም የአሲምባ ድረገጽ አዘጋጆች ብሎም የኢሕአፓ አመራር ነን የሚሉ ቁንጮ ትርፍራፊ እንዲህ ያለ ተራና ውዳቂ ዘለፋ በመሰንዘራቸው ምን ያህል ተስፋ እንደቆረጡና ራሳቸውን ለማጽናናት፤ ገንቢ አጀንዳ ከማቅረብ ይልቅ ‘አህያውን ፈርተው ዳውላውን’ የሚለውን ያበው ቢሂል የተየያዙት ይመስላል። 5 5 ውሸት ፬፡ “ወያኔ ስልጣን እንደያዘ ገላውዲዮስ ወያኔን የሚያስደስትና የሚጠላውን አማራና ኢሕአፓን የሚያወግዝ መጽሐፍ አሳተመ”። ምላሽ፡አደመ የ ‘ስራ ያጣ መነኵሴ ቆቡን ቀዶ ይሰፋል’ አይነተኛ ምሳሌ ነው። ስራ ያለው አይመስልም፤ ውሸትን እያላመጠና እያኘከ ብቻ የሚኖር ነው የሚመስለው። ይህ አሉቧልታ በ2008 እአአ አውግቸው ያለው ነው። መጽሐፌን ያነበበ ሁሉ ግን እያንዳንዱ ምዕራፍ አንጻራዊ ትንታኔ የያየዘና ሚዛን የጠበቀ ነው። ለምሳሌ አንዱ ምዕራፍ ስለ ‘ኢሕአፓና የኢትዮጵያ የግራ ክንፍ ሃይሎች’ የሚል ሆኖ ስለ ፓርቲው ጠንካራና ደካማ ጎኖቹን የሚያትት ነው። በተጨማሪ በዚሁ ምዕራፍ ‘ኢሕአፓ ከሌሎች ፓርቲዎችና ግንባሮች የነበረውን ግንኙነት’ አስመልክቶ ይተነትንና ያላንዳች አድልዎ የነበራቸውን ዝምድና በግልጽ ያስቀምጣል። አንድ የተማረ ሰው ማድረግ ያለበት ደግሞ ይኸው ነው። አደመና አውግቸው ስለዚህ ጉዳይ እኔ ያለኝ አመለካከት የጻፉት አይን ያወጣ ውሸት ነው። የአደመ ከአውግቸው ለየት የሚያደርገው ነገር ቢኖር “አማራን እንደምጠላ” የሚል ሐረግ ስላከለበት ነው። ቀደም ብየ እንደጠቀስኩት እኔ ለማንም ብሔር ጥላቻ የለኝም፤ ሁሉንም የኢትዮጵያ ብሔሮችና ብሔረሰቦች እንዲሁም ሁሉንም የአፍሪቃ ሕዝቦች የማፈቅርና የማከብር ሰው ነኝ። ምናልባት እነ አደመን ያወካቸውና ያናወጣቸው ነገር ቢኖር ያ ምልአተ ሕዝቡን (ሁሉንም የኢትዮጵያ ብሔሮች) አሰልፎና አቅፎ የነበረ ኢሕአፓ ባሁኑ ጊዜ ወደ ጎሳ ፖለቲካ ማዝቀጡና እርቃኑም ስለቀረ ሊሆን ይችላል። እኔ ለድሮው ኢሕአፓ ትልቅ ከበሬታ ነው ያለኝ፤ ምክንያቱም፦ ፩) ፓርቲው የሕዝብ ፓርቲ ስለነበር፤ ፪) ፓርቲው አያሌ ጀግኖች የወደቁበት ታጋይና አብዮታዊ ድርጅት ስለነበር ነው። ውሸት ፭፡ “የወያኔን ኮሜንተተር መጽሔትም ዋና አዘጋጅ ሆኖ የወያኔን ፕሮፓጋንዳ አሰራጨ” ምላሽ፡ ይህ አሁን በአደመ በ2015 የተጻፈው በ2008 በአውግቸው እንዳለ ቃል በቃሉ የተጻፈ ነበር። ግን ሙሉ በሙሉ ውሸት ነው። በእርግጥ በ Ethiopian Commentator አንድ አራት ድርሰቶች ስለ ዴሞክራሲ አጠቃላይ ታሪካዊ አመጣጥ እና የፈደራል ስርአት (አወቃቀር) በኢትዮጵያ እንዴት መገንባት እንደሚቻል ታሪካዊና ሂሳዊ በሆነ መልኩ አቅርቤ ነበር። ከዛ በተረፈ ‘ዋና አዘጋጅ’ ሆኜ አላገለገልኩም። ዋና አዘጋጁና ባለቤቱ ኃይለማርያም አበበ ይባላል፤ በመጽሔቱም ያሰራጨሁት አንዳችም ፕሮፓጋንዳ የለም። ቢኖርማ እነ አደመ በአግባቡ ይጠቅሱት ነበር። ውሸት ፮፡ “ወያኔ ሊሰግዱለት ያሉትን ያባርራል - ቂም አይረሳም…ለገላውዲዮስም የተለየ መልክ አላሳየውም፤ ወግድ፤ በዛው በርቁ ነው ያለው”። ምላሽ፡ ይህ የሚያስገርም ውሸት ቢሆንም እነ አደመ በወሬ የሰሙትና ያገኙት መረጃ ሊኖር ይችላል የሚል ግምት አለኝ። አሁን ያለው መንግሥት (ወይም ግለሰብ ባለሥልጣናት) ከአንዴም ሁለቴም ለአንዳንድ የስራ ሐላፊነት ጠይቀውኝ ነበር። ወግድ አላሉኝም። እኔ ግን የራሴ እምነት፤ አመለካከትና አካሄድ ስላለኝ ጉዳዩን በጥሞና መረመርኩትና ባለሁበት እንድጸና ወሰንኩኝ። እነሱም አልገፉበትም። ግን ብቀበለውና እነሱም ቢገፉበት ኖሮ ለሃገሬና ለሕዝቤ ነበር የምሰራው፤ ሃገርና ሕዝብን ማገልገል ደግሞ የመሰለ ፀጋ የለም። ለአንድ መንግሥት ማጎብደድና ለሃገር ማገልገል እጅግ በጣም የተለያዩ እሴቶች ናቸው። ውሸት ፯፡ “ገለውዲዮስ አማራን እንደሚጠላ በብዙ ጽሑፎቹ ግልጽ አድርጓል” 6 6 ምላሽ፡ እነ አደመ ‘ውሸት ቢደጋገም እውነት ይሆናል’ በሚል ፈሊጥ ያለ የሌለውን ይቀባጥራሉ። አማራን መጥላት አስመልክቶ ግልጽ ስላደረግኩት እዚሁ መድገሙ አስፈላጊ አይሆንም። ነገር ግን እነ አደመ ይኸን ዓይነት ውሸት እንደ የትግል ስልታቸው የያዙት ይመስላል። ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በዳያስፖራ ኢትዮጵያውያን ተቃዋሚ ኃይሎች በሚባሉ ዘንድ “ወያኔ ደርግን ያቸነፈው አማራን በማጥላላት ነውና እኛም ተመሳሳይ ስልት ብንጠቀም ግባችንን ልንመታ እንችላለን” የሚል ኢርትአዊ አስተሳሰብ ተሰራጭቶ ነበር። እኔ በበኩሌ ይህ አይነት አስተሳሰብ የተሳሳተ መሆኑን ጠቁሜ ነበር። አንድ ሐቅ መገንዘብ ያለብንና ወደድንም ጠላንም መቀበል ያለብን ነገር ቢኖር ወያኔ ሥልጣን የጨበጠው ደርግን በጦርነት በመውጋትና በማቸነፍ ነው። ውሸት ፰፡ “ወያኔ ለኢትዮጵያ የመጣ ዴሞክራስያዊ መፍትሔ ነው ያለውና ሀገር ውዳድ ሃይሎችን ያወገዘው ማን ነው?ገላውዲዮስ! ትግራይ የምትኮራባቸው ልጆች አፍርታለች” ምላሽ፡ እነ አደመና የአሲምባ ደረገጽ አዘጋጆች የተደናበሩ ፖለቲከኞች ስለሆኑ ነው እንጂ የኔ መጻሕፍትና ጽሑፎች ብያነቡ ኖሮ ይኸን ዓይነት ውሸት አይዋሹም ነበር። ግን ‘በደንባራ በቅሎ ቃጭል ተንጠልጥሎ’ እንደሚባለው ሁሉ እነኚ የኢንተርነት ጀግኖች ራሳቸውን ብቻ ሳይሆን ሕብረተሰባቸውን ጭምር እየጎዱ ይገኛሉ። በቅርቡ ታትሞ የወጣውን መጽሐፌ ብያነቡት ኖሮ የመጀመርያው ክፍል በኢትዮጵያ ዴሞክራሲ እንደሌለ ነው የሚገልጸው። በሌሎች ምዕራፋት ግን አንዳንድ አሁን የተደረጉት ክንውኖች ማለትም እንደ መሰረተ ልማት እና የዩኒቨሪስቲዎች መስፋት እንደ የኢትዮጵያ አወንታዊ ገጽታ አድርጌ አቅርቤዋለሁ። እኔ በበኩሌ ሃገር ወዳዶችን አላወገዝኩም፤ ግን ባሁኑ ጊዜ እምብዛም የማይናገሩና የማይዶሉቱ ኢትዮጵያውያን ካልሆነ በስተቀረ ተቃዋሚ ነን ብለው በጎሳ የተደራጁና የሚንጫጩ ስብስቦች ውስጥ ‘ሃገር ወዳድ’ አሉ ለማለት ያዳግተኛል። መደምደምያ፦ አገራችን ኢትዮጵያ የሁሉም ኢትዮጵያዊ፤ማለትም ከዛላምበሳ እስከ ሞያሌ፤ከመተማ እሰከ ጭናግሰን ሱማሌ ጠረፍ፤ ከአሶሳ እስከ ጂቡቲ ጠረፍ ያለውን ሕዝብ ኩራት ናት። ለሁሉም ጥቁር ሕዘቦች የነጻነት ችቦ መናኸርያ ናት። የኢትዮጵያ አንድነትና ልዓላዊነት መጠበቅና መንከባከብ የምንችለው ግን ኢትዮጵያዊነትን ስናጎለምስና የጎሳ ፖለቲካን አጥብቀን ስንቃወም ብቻ ነው። የትምክህተኝነትና ጠባብ ብሔርተኝነት ስሜት ኢትዮጵያችንን በትልቅ አደጋ ውስጥ ሊያሰምጣት ስለሚችል ኢትዮጵያ-አቀፍ ድርጅቶችና ተቋማት እንደገና ማቋቋም ታሪካዊ ሃላፊነታችን ይሆናል። ለዚሁ ተግባር ቅድመ-ሁኔታ የሚሆነው ግን አመለካከታችን ኢትዮጵያዊ ሲሆን ብቻ ነው። ማንኛውም ኢትዮጵያዊ ማንንቱን ሲጠየቅ የመጀመርያና ተቀዳሚ መልሱ “ኢትዮጵያዊ ነኝ” መሆን አለበት። በሁለተኛ ደረጃ ‘ከየት ብሔር ነህ/ነሽ ተብሎ/ላ ከተጠየቀ/ች ደግሞ መልሱ “ኢትዮጵያዊ ነኝ” መሆን አለበት። የኢትዮጵያ ብሔር ብሔረ-ሰቦች አንድ የሚያደርጋቸው ነገር ቢኖር የጋራ መለዮአቸውን የሆነውን ኢትዮጵያውነት ነው። ስለሆነም ኢትዮጵያን የሚያደሙና አንድነቷን የሚጻረሩ የትምክህትና ጠባብነት ጣምራ አደጋዎችን እናስወግድ። ኢትዮጵያውነትን እናንግስ። ኢትዮጵያ በአንድነቷና በጻነቷ ለዘልአለም ትኑር! የጸሐፊውና የአፍሪቃ ልማትና ትምህርት ተቋም (አልትተ) መብት በሕግ የተጠበቀ ነው. All Rights Reserved. Copyright © Institute of Development and Education for Africa (IDEA) 2015. ለአስተያየትና ገንቢ ነቀፌታ በ dr.garaia@africanidea.org መልእክት መላክ ይችላሉ።

     Give your opinion.