Discussion Forum

 ሰብአዊና ዜግነታዊ ግዴታችንን በተግባር የምናሳይበት ጊዜው አሁን ነው።

ሰብአዊና ዜግነታዊ ግዴታችንን በተግባር የምናሳይበት ጊዜው አሁን ነው።

የብዙ ብሔርና ብሔረሰቦች እናት የሆነችው አገራችን ኢትዮጲያ ፖለቲካ፣ ሃይማኖት፣ ቋንቋ፣ ዘር ሳይከፋፍላት አንድነቷን ጠብቃ የቆየች፤ እንዲሁም ምንም አይነት የውጭ ጠላት ሳይደፍራት እስከ ዛሬ ድረስ ዳርድንበሯን አስከብራ ታሪክ ሲያሞግሳት የኖረች ክቡር አገር ናት። ዛሬ እያንዳንዱ ዜጋዋ በተወለደበትና ባደገበት ቀየውና መንደሩ፦ ማንነቱ፣ ቋንቋው፣ ሃይማኖቱ፣ ባሕሉ፣ ወጉና ሥርዓቱ ተከብሮለት ራሱን በራሱ እያስተዳደረ፣ የተሻለችና የበለፀገች ኢትዮጲያን ለመገንባት በምያስችል በመልካም ጎዳና ላይ ነው።

 ቀደም ሲል በነበሩት መንግሥታት ሕዝቡ በዜግነት የተመዘገበው ለግብር፣ ለምርጫና ለውትድርና አገልግሎት ብቻ፤ ነገር ግን በአገሪቱ ውስጥ በምካሄደው በትምህርት፣ በምርትና በፖለቲካ ጥቅሞች ላይ ተጋሪ ሳይሆን አያሌ ዘመናትን አስቆጥሮ ነበር። 

 የቀድሞ ነገሥታትና መሪዎች (መኳንንት፣ መሳፍንትና የኢሠፓ ፓርቲ መሪዎች) አገልጋይና የጥቅሙ ተካፋዮች የነበሩ ካድሬዎች ብሎም ምንም ያልገባቸው ጥሬና ጭፍን የሆኑ የወሬ ጀሌዎች (የግብፅ፣ የቱንዝያ፣ የሊቢያ፣ የስሪያ፣ የዮርዳኖስና የየመን ወዘተ... የፓልቶክ፣ የፌስብክና የዩቱዩብ አጃቢ አይነቶች) ከላይ በተነሱ ሃሳቦች ላይ አይስማሙም፤ ምክንያቱም ግማሾቹ ጥቅማቸው ስለተነካ ከፊሉም ደግሞ መብታቸውንና ግደታቸውን እንዲሁም ፖለቲካውን ከኢኮኖሚው ለይተው የማያወቁ ጥፍጥፍ ሥርዓተ-አልበኞችና ለሆዳቸው ያደሩም አልጠፉም።

 ለኔ ኢትዮጲያዊነት ማለት፣ ባለው መንግሥት የኢኮኖሚ ፕላን ተደግፈን የምንወዳትን አገራችንን ከራሐብ፣ ከርዛት፣ ከጥማት እና ከኋላቀርነት አውጥተን ዳር ድንበሯ ተከብሮና እግዚአብሔር በተፈጥሮ ለሰው ልጅ የለገሰውን ሰበአዊ የዜግነት መብቱ፣ ቋንቋው፣ ወጉ፣ ባሕሉና ሃይማኖቱ ተከብሮለት መኖርን ነው።

 የአንድ አገር መሠረቱ ልማት ነው። ካፒታል የሌለው አገር ፖለቲካን መምራት አይችልም።  ማናችንም እንደ ምናውቀው ከውጪ ከመጡ ጠላቶቻችን  በላይ እስከ ዛሬ የጎዳን ነገር ቢኖር ድህነት መሆኑ አያጠያይቅም። በማናቸውም መስክ የአገራችን ዜጎች የምያስመዘግቡት ድሎች የራሳቸው ድል ብቻ ሳይሆን በየትኛውም የዓለም ክፍል ላለው ኢትዮጲያዊ ዜጋ ሁሉ መኩሪያው ነው። ዛሬ በአገራችን በሚካሄደው በልማት ጎዳና ሁላችንም ደስ ብሎን ልማቱን ማፋጠን ሲገባን፣ የሆነውንና ያልሆነውን የእያቀላቀልን በለስላሳና በመርዛማ አንደበታችን የተደበቀውን የበቀል እንኩሮ በትኩስ ውሃ እየበጠበጥን በንፁሃኑ ሕዝብ መሀል እየረጭን ለብዙ ዘመናት በረሃብና በርዛት የተጎዳውን ደሃውን ሕዝባችንን ደግመን ደጋግመን ማቁሰሉ ተገቢ አይመስለንም።

 በውሸት ተፈጥረው በውሸት ያደጉ በውሸት የተደራጁ አንዳንድ ድርጅቶች ተቃዋሚ በመሆናቸው ለማንም ባያስገርምም (ተቃዋሚ ማለት ጦርና ጋሻን ይዞ የገዛ ሕዝቡን መውጋት ሳይሆን፣ መርህ አላማ በሆነው ሕጋችን ላይ የተመረኮዘና ዘመናዊ በሆነው በጠረጴዛ ዙሪያ ክርክር ላይ ያመነ መሆን ስገባው)፤ እነርሱ በስመ-አንድነት የራሳቸውን የዘረኝነትና የጥላቻ መረባቸውን ዘርግተው እንደ እባብ መርዛቸውን በየቤተክርስቲያኑ፤ በየመስጊዱና በያለበት በሕዝብ ሚድያዎች ሲረጩ አይተናል። ያልቻሉት ነገር ቢኖር የሁሉ ነገር ባለቤት የሆነውን የሰፊውን ሕዝብ አእምሮ ብቻ ነበር። የተበደለው ሕዝብ ራሱ ተበድሎ እያለ ለአገሬ ሲል ይቅርብኝ ችዬ ልለፍ ብሎ ሲለምን፣ በአንፃሩ አስገራሚው ድራማ፣ በዳዩ (መጥፋት የማይቀርለት) አይ አሻፈረኝ ብሎ ሁከት ለመፍጠር ወዲያና ወዲህ መወራጨቱ ነው።

 

አንዳንዶች ደግሞ ያለውን ልማታዊ መንግሥት ደጋፊም ሆነው ሳለ ግን “ሕጋቸው ውልቀ ክብራቸው ብሎም እልሃቸው ደግሞ ሃይማኖታቸው” ያደረጉ ክብራቸውን ከተጠቃሚው ከኢትዮጲያ ሕዝብ በላይ አድርገው የሚመለከቱ ያዙኝ ልቀቁኝ የሚሉ ምንም ያልገባቸው የመንግሥትን ቀና አመለካከት እንዳለ ወደ ሕዝቡ ማስተላለፍ ያልቻሉ ወልጋዳና ደካማ አየር በአየር የፖለቲካ ነጋዴዎችም አልጠፉም። ዛሬ ህዝባችን በሚገኝበት የህዳሴ ዘመን ፤ "አንድ እንደ ሺ ሺም እንደ አንድ ሆኖ" ልማት አላማዉ የሆነ ህዝብ እንጂ ያረጀና ያፈጀውን ጦርነትን ካለመፈለጉም አልፎ፣ ጦርነቱን ከረሐብና ከችጋር ጋር አድርጎ በሚታግልበት በአሁኑ ወቅት ዜጋ ነኝ የሚል ሁሉ ፤ በዚህ ቅዱስ ዓላማ የሚሳተፍበት ጊዜው አሁን ነው። መተለም የሚገባን ማንም ካቆመበት መቀጠል የሚያስችል ረጅም የመቶ ዓመት ዕድሜ ያለው ቀና ዕላማ እንጂ ቁንፅልና ቆርጦ ቀጥል ፖለቲካ የምናካሂድበት ጊዜው አልፎአል።

 

መማር ማለት እያንዳንዱ ያለበትን የአገር አደራና ሀላፊነትን በአገሪቷ ሕግ መሠረት ተወጥቶ መገኘት እንጂ፣ የተማሩበትን ጊዜና ገንዘብ ያጠፉበትን ታላቁን የሙያ ዲግሪያቸውን ዋዛ በማድረግ ሳይጠቀሙበት ሲቀሩ ማየት ደግሞ ወይ አለመታደል ያሰኛል።

 የኢትዮጲያ ሕዝብ ጥያቄው ጠግቦ በልቶ፣ ሳይበርደው ደርቦ፣ ጅብ ፈንግሎ የማይገባበት ጠንከር ያለ ግድግዳ ባለው መጠለያ ውስጥ መኖርን፣ በጎማ ጫማ ለዘጠኝና አሥር ሰዓታት የምኳትንበትን መንገድ በዘመናዊ ትራንስፖርት መተካትን፤ በየቀኑ ለቤት ሥራ፣ ለማገዶ፣ ለእንጨት ማምረቻ ፋብሪካዎች እየተቆረጠ የሚያልቀውንና የተፈጥሮን የአየር መዛባትን ለመቆጣጠር የምያስችለውን የዛፎችን ሕይወት በማዳን ብሎም ዝናብ ወቅቱን ጠብቆ እንዲመጣ ማድረግን ነው።

 ከዛሬ ሃያ አመት በኋላ የኢትዮጲያ ሕዝብ ቁጥር እስከ ሁለት መቶ ሚሊዮን ይደርሳል ተብሎ ይገመታል፤ ታዲያ ዘጠናውን ሚሊዮን መመገብ ካልቻልን እንዴት ሁለት መቶ ሚሊዮኑን መመገብ እንችላለን? በታሪክ እንዳየነው የየትኛውም አገር ሕዝብ በአገሩ እኮኖሚ ላይ አምፆ አያውቅም። ታዲያ በስመ ፖለቲካ ድህነታችን ደካማ ጎናችን መሆኑን የምያውቁ ወገኖቻችን ደግመው ደጋግመው (“በሰው ቁስል እንጨት ስደድ”) ያንን ቁስል ማጥቃቱ ብልህነት አይመስለንም። እያንዳንዱ ኢትዮጲያዊ በውጪው አለም ላይ ያለው ሆነ በሃገር ውስጥ ያለው ሁሉ፣ የሕዝባችንን ጥያቄ የምንምልስበት፣ መብታችን ብቻ ሳይሆን የዜግነት ግደታችንም ጭምር መሆኑን አውቀን ሃላፊነታችንን ልንወጣው ይገባል!! ዋጋ ቢስ የሆነውን ደካም የፕሮፖጋንዳ ኮርጆን ከመሙላት ይልቅ ዘላቂነት ባለው በአገራችን ልማትና በገዛ ራሳችን ጥቅም ላይ የምናተኩርበት ብሎም በታሪክ ከመተፋት የምንድንበት ወቅቱ አሁን ነው።

ፖለቲካን በየቤተክርስትያናችንንና በየመስግዶቻችን ደብቀን ይዘን ገብተን ሕዝቡን ማበጣበጡን ርግፍ አድርገን የምንተውበት ጊዜው አሁን ነው። ልዩነታችን አንድነታችን እንጂ የመከፋፈያ መሠረት ሊሆን አይችልም። አንዳንዶቻችን ደግሞ የዲሞክራሲ መብታችን ተከበረልን ሲባል ጭራሽ ጋጠ ወጥ (anarchism) ባህርይ በመላበስ ፣ የማይረባውን የመከፋፈል ዝባዝንከ መለፍለፉ የምያከሳን እንጂ የምያደልበን አይደለም።አንዳንዶች ደግሞ በዚህ ሞገድ ውስጥ ተዘፍቀው ራሳቸውን ካጠመቁ በኋላ ሕዝቡን በራሳቸው አመለካከት ጠልፈው ለመጣል ሲሉ ራሳቸው እዚያው ጭልጥ ብለው መቅረታቸው ብቻ ሳይሆን ከማይጠፋው ከኢትዮጲያ ሕዝብና መሬቷ መሸሸግ አለመቻላቸው ትልቅ ውርደታቸው ነው።

 

ማሳሰቢያ

ክቡራትና ክቡራን ስዱድ ሰብአዊና ዜግነታዊ ሃላፊነት የሚሰማችሁ ወገኖች ሁሉ! በአገራችን በሚካሄደው በማናቸውም የልማት ሥራ ላይ ገብተህ ወይም ገብተሽ ጊዜው ሳያመልጣችሁ ገንዘባችሁን እንቬስት የምታድርጉብት ወቅቱ ስለሆነና ባንሳተፍ ግን ተረትና ታሪክ ሆኖ መቅረትም ጭምር እንዳለ እንዲታውቁ ነው። በዚህ በካልጋሪ ከተማ ውስጥ በሚገኙ ከአባይ ግድብና ከአገራችን ልማት ጋር ትብብር ካላቸው ድርጅቶች (ከነኢትዮ-አባይ ልማት ማህበር፣ ከነኢትዮ-ካልጋሪ ለአባይ)  ጋር በመተባበር ቀርባችሁ በአገራችሁ እንቬስትመንትና በአባይ ግድብ ግንባታ ድጋፍ በመስጠት አገራችሁን እንዲትረዱ እናሳስባለን። አንዳንድ የታሪክ አተላዎቹ እንደሚያወሩት መደለያ መስሎአችሁ ጊዜው እንዳያልፍባችሁ ነገር ግን ያልንዳች ጥርጣሬና ዩልኝታ እውነታውን እንድትረዱ እያስገነዘብን በምትወዷት በእናት አገርራችሁ ጉዳይ ሁሉ ላይ በመሳተፍ አገራችሁን ከረሐብና ከርዛት እንዲታወጧትና በዚህ ታሪካዊ ተግባር ላይ እንድትሣተፉ ይህንን ታላቅ ሃገራዊ ጥሪ እናቀርባለን!! 

            ካልተሣፈሩበት ቶሎ ተሽቀዳድሞ፣

          ጊዜ ታክስ አይደልም አይጠብቅም ቆሞ!!!!

     Give your opinion.