Discussion Forum

 የማዶላ ቡቱቶ ጽሁፍ፣ የጋሞ ሕዝብ የተቃውሞ እንቅስቃሴ እና ቀጣዩ የመልስ ፍለጋ ጉዞ

የማዶላ ቡቱቶ ጽሁፍ፣ የጋሞ ሕዝብ የተቃውሞ እንቅስቃሴ እና ቀጣዩ የመልስ ፍለጋ ጉዞ
ጤና ይስጥልኝ ውድ አንባቢያን!
በቅርቡ አቶ ታደለ ቱፋ በተባለ ግለሰብ ተጽፎ የወጣውና ልክ እንደ ፀሐፊው አባት ስም ትርጉም የፅሑፍ ቡቱቶ የሆነው አንድ ጥራዝ በፈጠረው ትኩሳት (ቱፋ ማለት በፀሐፊው የትውልድ አካባቢ አነጋገር ቡቱቶ መሆኑን ልብ ይሏል) ከፍተኛ የተቃውሞ እንቅስቃሴ በጋሞ አካባቢና በሕዝቡ ዘንድ መፈጠሩን እና በዚህም መነሻ ከተለያዩ የማህበራዊ ድረ-ገጽ ተጠቃሚዎች የተለያዩ ይዘቶችና መልዕክቶች ያሏቸው መጣጥፎች እየተለቀቁ መሆኑን እንደ አንድ አንባቢ ታዝብያለሁ፡፡ የሕግ ምሁራንና ባለሙያዎች “Injustice anywhere is a threat to justice everywhere,” እንዲሉ የታደለ ቱፋን ቡቱቶ ጽሑፍ ላነበበ እና ከበስተጀርባው አሉ ተብለው በሚዲያው እየተለቀቁ ያሉ ጉዳዮችን ላጤነ አንድ ሚዛናዊ አስተሳሰብን ለሚከተል አዕምሮ ይህንን ጉዳይ በዝምታ ማለፍ ኢፍትሐዊነትን መተባበር መስሎ ታይቶኛል፡፡ እኔም እንግዲያውስ (ሚዛናዊ አስተሳሰብ አለኝ ብለው “ከሚደሰኩሩት” መሐከል መሆኔ ይያዝልኝ) በዚሁ መርህ ተመርኩዤ ኢፍትሐዊነትን የመተባበርን ካምፕ ከመቀላቀል የሚያስመልጡኝን የሰማኋቸውንና የማውቃቸውን መረጃዎች ለውድ አንባቢያን በማካፈልና ፍትሕ ተገቢ ቦታዋን እንድታገኝ ያስችላሉ ብዬ የማምንባቸውን አስተያየቶቼን በመሰንዘር የተግባራዊ ተሳትፎ ‘ሀ፤ሁ‘ዬን ልጀምር ወደድሁ፡፡ እነሆ ትቀበሉኝ ዘንድ መልካም ፈቃዳችሁ ይሁን!
አለመታደል ሆኖ (ከፀሐፊው ታደለ ቱፋ ስም በተቃራኒ ማለት ነው) የጉዳዩ ጣራ (ክላይማክስ) የታደለ ቱፋ ማዶላ ሆነ እንጂ (በነገራችን ላይ ታደለ ዶሳ የሚባል ሰውም ጽሁፉን በመቦተቱ ሥራ እጁ አለበት ይባላል) የጉዳዩ ሥረ-ግንድ በቀደም የጋሞ ጎፋ ዞን አስተዳደር በጠራው ሚኒ-ኮንፍራንስ ላይ አንድ የሐገር ሽማግሌ እንዳሉት በጎፋ ዞን የምኞት መንፈስ ዙሪያ የሚሽከረከር ሆኖ ይታያል፡፡ ለግንዛቤ ይሆን ዘንድ በኮንፍራንሱ ላይ የሐገር ሽማግሌው እንዲህ ነበር ያሉት፤”የጎፋ ዞን ጥያቄ ውቃቢያችሁ በተነሳ ቁጥር እስከ መቼ ይሁን እኛ የምንሰደበው?“ በእውነት ከታላቅ ግንዛቤ የሚመነጭ አባባል ነው! ሽማግሌው ሁኔታዎችን ምን ያህል በጥልቀት አጢነው እንደተናገሩት በወቅቱ አስገርሞኛል፡፡ እኔም የእኚህን ሰው ሀሳብ እጋራለሁ፡፡
ትርፉ ምን እንደሆነ አድራጊዎቹ በይበልጥ የሚያውቁት ቢሆንም እውነትም የጎፋ ዞን ጥያቄ አቀንቃኞች የአቀንቃኝነታቸውን ልክ ለአለቆቻቸው የሚያረጋግጡበት መሥፈርት የጋሞ ብሔርን እንደ ሕዝብ መስደብ መሆኑ ተደጋግሞ እየታየ ይገኛል፡፡ ይህንም ያደረገ ሰው አቀንቃኝነቱ ተረጋግጦ ባጠረ ጊዜ ውስጥ ሹመት ይሰጠዋል፡፡ ታዲያ ደምና አጥንታቸውን ከስክሰው አገሪቷን ከጭቆና ነፃ ያወጧት ታጋዮች እንኳን አብዛኞቹ ያለሹመት በሚኖሩበት ሥርዓት ሕዝብን መስደብ ብቻ ሹመትን የሚያስገኝ ከሆነ ተሳዳቢዎቹ ለምንስ አይሳደቡ፤ ለምንስ ስድብን የቡቱቶ ጽሑፋቸው ማጀቢያ አድርገው አያወጡት! በቀጣይ ጊዜ ከአድራጊ ፈጣሪ አለቆቻቸው ሹመት ይጠብቃቸዋላ! 
ታዲያ እነ ማን በምን ጊዜ ምን አድርገው ተሹመው ነበር? የምትለዋ ጥያቄ መቼም በአንባቢያን አዕምሮ መመላለሷ የሚቀር አይመስለኝም፤ እኔም ራሴ ይህችኑ እጠይቅ ነበርና፡፡ በዚህ ዙሪያ መረጃ ብቻ ሳይሆን ተጨባጭ ማስረጃም ጭምር የሚያቀርቡ አካላት በብዛት አጋጥመውኛል፡፡ ለምሳሌ ማስረጃ አቅራቢዎቹ እንደ ጥሩ አስረጅ ከሚያቀርቧቸው ክስተቶች መሐከል የሚከተሉት ይገኙባቸዋል፡፡
1. በ1995 ዓ.ም በደኢህዴን ዳግም ተሐድሶ ወቅት አንድ ምሁር ነኝ ባይ የጎፋ ተወላጅ “ጋሞ የጎፋ ቅድመ ግንድ ቅጥያ ሆኖ ጎፋን ግም አሰኝቷል“ የሚል ትምክህት አዘል የስድብ ቃል በጋሞ ብሔር ላይ ተናግሮ በዚሁ ምክንያት ተገምግሞ ከድርጅቱ ከተባረረ በኋላ አንድ አመት በማይሞላ ጊዜ ውስጥ የሳውላ ከተማ ከንቲባ ሆኖ ተሹሟል፡፡ ልብ በሉ እንግዲህ፡- ጋሞን ከመስደቡ በፊት ይህ ግለሰብ የከንቲባ ደረጃ ሹመት አልነበረውም፡፡ ከስድብ ድርጊቱ በኋላ ግን ለላቀ ሹመት በቅቷል፡፡
2. ይህ አዛዜ አልዬ በሚል ስም የሚታወቀው ግለሰብ እዚህም የሹመት ቦታ ላይ ሲሠራ በፈፀመው የኪራይ ሰብሳቢነት ተግባር ተገምግሞ ከተባረረ በአንድ ዓመት ልዩነት አሁን ደግሞ የክልሉ የግብርና ቢሮ የኦዲት ሀላፊ ሆኖ በመሾሙ በአሁኑ ወቅት በዚሁ ሹመት ቦታ ላይ እየሠራ ይገኛል፡፡ የጎፋ ዞን ጥያቄው ቃል ኪዳን እስካለ ድረስ ቀኝም ወደቀ ግራ ዕድገት እንጂ ውድቀት አያገኘውማ!
3. በ2004 ዓ.ም የሳውላ ከተማ አስተዳደር የመንግስት ኮሚኒኬሽን ሐላፊ የነበረ በዛብህ በላይነህ የተባለ ሌላ የጎፋ ተወላጅ “የጋሞ ብሔር ታሪክ የለውም“ የሚል የእብሪት መልዕክት ያለውን ጽሑፍ በመጽሔት አዘጋጅቶ በማቅረቡ ምክንያት ተገምግሞ ከተባረረ በኋላ በአጭር ጊዜ ውስጥ እንደገና ተጨማሪ ዕድገት ተሰጥቶት የገዜ ጎፋ ወረዳ ዋና አስተዳዳሪ ሆኖ በመሾሙ በአሁኑ ሰዓት ወረዳውን እያስተዳደረ ይገኛል፡፡ ይህም ግለሰብ ቢሆን ከስድብ ድርጊቱ በኋላ ከፍ ወዳለ ሹመት መሔዱን ልብ በሉልኝ፡፡ 
4. የቀድሞው የጋሞ ጎፋ ዞን ግብርና መምሪያ ኃላፊ የነበረው ጋንታ ጋምአ የተባለ የጎፋ ተወላጅ ባሳየው ብልሹ አመራር ምክንያት በዞኑ አርሶ አደር ዘንድ በተለይም በጋሞ አካባቢ በዘረጋው ስውር የፀረ ምርት ደባ ዕድገትን ሳይሆን ድህነትን በማስፈኑ ሲገመገም እስከ ጥሬ ቃሉ “ከአርሶ አደሩ ማንቁርት እራስህን አላቅ!“ ተብሎ ከሥልጣን የወረደ ቢሆንም ይህ ድርጊቱ ሊያስጠይቀው ሲገባ ሌላ ሽልማት አግኝቶ በመንግስት ወጪ የማስትሬት ትምህርቱን እንዲማር ተልኳል፡፡
5. ይህ ግለሰብ የማስትሬት ትምህርቱን ጨርሶ ወደ ዞኑ በተመለሰ ጊዜም በአለቆቹ በኩል ዳግም ለዞኑ የፀጥታና አስተዳደር መምሪያ ሐላፊነት ታጭቶ ነበር፡፡ ሆኖም የቀድሞ ድርጊቱን የሚያውቁና ከጎፋ ዞን ጥያቄ ሰንሰለቱ ውጪ የሆኑ ጥቂት የዞኑ አመራር አባላት ተቃውሞ በማሰማታቸው የመምሪያ ሀላፊነት ዕቅዱ ከሽፏል፡፡ ይሁን እንጂ አሁንም የቃል ኪዳኑ አለቃቸው በደኢህዴን ጽ/ቤት ያለውን ከፍተኛ ስልጣን በመጠቀም ግለሰቡን ወደ ክልል በማሻገር የክልሉ የገጠር ሥራ ዕድል ፈጠራ ኤጀንሲ ሐላፊ አድርጎ በማሾሙ ይህ ግለሰብ በአሁኑ ሰዓት በተሸመበት ቦታ አመራር እየሠጠ ይገኛል፡፡ የዞን ጥያቄው ቃል ኪዳን አባላት ፀረ-ሕዝብ ድርጊት ቢፈጽሙም ከጥቂት የማዘናጊያ ወራት በኋላ ተመልሰው ይሾማሏ!
6. ጋሞነትን የሚጎዱ ሐሳቦችን በማራመድ እንደሚታወቅ የሚነገርለት የቀድሞው የጋሞ ጎፋ ዞን ም/አስተዳዳሪና የሲቪል ሰርቪስ መምሪያ ኃላፊ የነበረው ታዬ ሰይፉ የተባለ የጎፋ ተወላጅ በአቅም ማነስ ተገምግሞ ከሥልጣን ከወረደ አንድ አመት ሳይሞላው የአርባ ምንጭ መምህራን ትምህርት ኮሌጅ ዲን ሆኖ ተሹሟል፡፡ ዋናው ነገር የአቅም መኖር ወይም አለመኖር ሳይሆን የቃል ኪዳኑ ታማኝ አባል ሆኖ መገኘት ነዋ! 
7. በመጋቢት ወር 2007 ዓ.ም የጋሞ ጎፋ ዞን የስፖርት ሻምፒዮና በገዜ ጎፋ ወረዳ ቡልቂ ከተማ በተዘጋጀበት ወቅት የጎፋ ዞን ጥያቄ አቀንቃኞቹ ያደራጁት የጎፋ ተወላጆች ቡድን ከጋሞ ወረዳዎች ለጨዋታው የሔዱ የስፖርት ልዑካንን ብሔራቸውን የሚያነቋሽሹ ስድቦችን ከመስደብም ባሻገር በጨዋታዎች ወቅት በሜዳ ውስጥና ከሜዳ ውጪ ድብደባ ፈጽሞባቸዋል፡፡ 
8. ከዚህ ቀደም ተመሳሳዩ ሻምፒዮና በሳውላ ከተማ በተዘጋጀበትም ወቅት ይህ ዓይነቱ ድርጊት ከጋሞ ወረዳዎች በሔዱ ልዑካን ላይ በተመሳሳይ ሁኔታ ተፈጽሞ ነበር፡፡ ይሁን እንጂ የድርጊቱ ፈፃሚዎች በጎፋ ዞን ጥያቄ አቀንቃኞች ሽፋን ስለሚሠጣቸው አንድም አይነት የሕግ ተጠያቂነት ተተግብሮባቸው አያውቅም፡፡ ይልቁንም ይሞገሱበታል፤ ይሸለሙበታል እንጂ፡፡ 
ውስጥ አዋቂ ምንጮችና በልዩልዩ ድርጅታዊ መድረኮች ተገኝተው ክስተቶችን በአጀንዳቸው የከተቡ አካላት እነዚህንና ሌሎች አስረጅ ሁኔታዎችን ያቀርባሉ፡፡ እኔ ደግሞ “ማርም ሲበዛ ይመራል” ነውና ብሒሉ ዝርዝሩን እዚህ ላይ ማቆም መርጫለሁ፡፡ እናንት ከፈለጋችሁ ሌሎቹን ልትጨምሩበት ትችላላችሁ፡፡
እናንተዬ፡- ይህን ሁሉ በሰማሁ ጊዜ አራት የግርምት ጥያቄዎች ተከሰቱልኝ፡፡
1. እነዚህ የቃል ኪዳኑ አባላት ይህንን አይነት ድርጊት እየፈፀሙ ያሉት ለምን ይሆን?
2. ለመሆኑ ይህ ሁሉ እየሆነ ያለው በአፍሪካ ደረጃ በጥንካሬያቸው ግንባር ቀደም ከሆኑ የፖለቲካ ፓርቲዎች አንዱ በሆነው ኢህአዴግ ውስጥ አባል ፓርቲ በሆነው በደኢህዴን ውስጥ እንደመሆኑ መጠን ደኢህዴንስ ራሱ ውስጠ ድርጅት አሠራሩ ምን ይመስል ይሁን?
3. የዚህ ዓይነቱ የጥፋተኞች የመም አሠራር መንግሥታዊ የአቋም መግለጫ የሆነ ያክል እንዲህ እስኪገዝፍ ድረስ ኢህአዴግሥ እንደምን ዝም አለው? 
4. እነዚህ ጉዳዮች የሚፈፀሙበት ዞን እስከ ስሙ ጋሞ ጎፋ ሲሆን በዚህ ዞን ደረጃና በተለያዩ የሀገሪቱ የአስተዳደር እርከኖች ላይ እንደ ጎፋ ሕዝብ ሁሉ የጋሞም ሕዝብ ተወካዮች ይኖሩታል ብዬ አምናለሁ፤ ይህ ሕገ-መንግሥታዊ ነውና፡፡ ታዲያ እነዚህ ተወካዮች አሁን እየተነሱ ያሉትን በጋሞ ብሔር ላይ የሚፈፀሙ የመብትና የጥቅም በደሎች እንደምን ቢያይዋቸው ነው በደሎቹ ያለ ተቃውሞ ድምፅ ይህን ያህል የገዘፉት? 
ደግነቱ ባነበብኳቸው፤በሰማኋቸውና በማውቃቸው ጉዳዮች ላይ በመንተራስ ለነዚህ ጥያቄዎች ተገቢ ትንተና ለመስጠት የሚጋብዙኝ የግርምት ሐሳቦችም ጭምር ተከስተውልኛል፡፡ እንግዲህ በሙሉ ጥሞና የማንበቡን ነገር አደራ እላችኋለሁ! ጥያቄዎቼንም እየራሳቸውን አስችለን አንድ በአንድ እንመልከት፡፡
1. እነዚህ የቃል ኪዳኑ አባላት ይህንን አይነቱን ድርጊት እየፈፀሙ ያሉት ለምን ይሆን?
መቼም በ21ኛው ክፍለ ዘመን ላይ ባለንበት በአሁኑ ጊዜም ቢሆን አንዳንድ ዕብድ ይጠፋል ባይባልም የዞን ጥያቄው ቃልኪዳን አባላት በሞላ ለጋሞ ብሔር ካላቸው ጥላቻና ክፉ ዓላማ በመነሳት ይህንን አስነዋሪ ተግባር እየፈፀሙ ያሉ ናዚዎች ናቸው ማለት ይከብዳል፡፡ ከዚያ ይልቅ የጋሞ ብሔርን እንደ ሕዝብ በመስደብ፤ በማዋረድና ክብሩን በመንካት የቃል ኪዳኑ አባላት የወጡበትን የጎፋን ሕዝብ የጋሞ ሕዝብ እንዲጠላው፤ ከሕዝቡ ጋር እንዲጋጭና በዚህም ምክንያት አብሮ የመኖር ዕድሉ እንዲቀጭጭ በማድረግ በቀደሙት አመታት የጎፋን ሕዝብ ቀስቅሰው ያልተሳካላቸውን የጎፋ ዞን ቅዠት የማሳካት ዓላማ አንግበዋል ባይ ነኝ፡፡ ይህ ደግሞ ከመነሻዬ የጠቀስኳቸው የኮንፍራንስ ተካፋይ የሐገር ሽማግሌ ካስቀመጡት አባባል ጋር መግጠሙን ልብ በሉ፡፡ “የጎፋ ዞን ጥያቄ ውቃቢያችሁ በተነሳ ቁጥር እኛ እስከ መቼ ነው የምንሰደበው?” ነበር ሽማግሌው ያሉት፡፡
“የጋሞ ሕዝብ ታዲያ ምኑ ሞኝ!” ወንድም የሆነውን የጎፋ ሕዝብ ሊጠላና ሊጋጨው ቀርቶ በክፉ የሚያነሱትን እንኳን ሊሰማ አልፈለገም፤ አይፈልግምም፡፡ ችግር ፈጣሪው ሕዝቡ ሳይሆን ሕዝቡን እንወክላለን የሚሉ በአጋጣሚ ሥልጣን በእጃቸው የገባና ያንን ተጠቅመው ክፋትን የሚያሰራጩ ጥቂት የቃል ኪዳኑ አባላት እንደሆኑ ጠንቅቆ ያውቃልና፡፡ በነገራችሁ ላይ ይህ የቃል ኪዳኑ አባላት ስብስብ በእጁ የገባውን ከፍተኛ የፖለቲካ ስልጣን በመጠቀም በጎፋ ወረዳዎችም የራሱን ፅንፈኛ አቋም የማይደግፉትን የጎፋ ልጆች ጭምር ከሥልጣን አባሮ እንደጨረሰ ይወራል፡፡ 
ያም ሆነ ይህ ከክፋት በስተቀር በጎ እሴትን ያልታደሉት ታደለዎች ቡቱቶ ዕሁፍም ሆነ የቃል ኪዳኑ አባላት እራሳቸውን እንደ አሜባ አባዝተው በጋሞ ጎፋ ሕዝብ ስም የወረዳ፤ የዞንና የክልል የፖለቲካ ሥልጣን ቦታዎችን መውረር እንደዚሁም የጋሞን ሕዝብ በስድብና በማንቋሸሽ የማበሳጨት ሙከራቸው ሕዝቡ ጨዋነቱን ጠብቆ አቤቱታውን ለመንግሥት ከማቅረቡ ውጪ ወዳልሰለጠነ አካሔድ ሊመራው አልቻለምና የቃል ኪዳኑ አባላት ከፍተኛ የፖለቲካ ኪሳራ ገጥሟቸዋል ባይ ነኝ፡፡ 
2. ለመሆኑ ይህ ሁሉ እየሆነ ያለው በአፍሪካ ደረጃ በጥንካሬያቸው ግንባር ቀደም ከሆኑ የፖለቲካ ፓርቲዎች አንዱ በሆነው ኢህአዴግ ውስጥ አባል ፓርቲ በሆነው በደኢህዴን ውስጥ እንደመሆኑ መጠን ደኢህዴንስ ራሱ ውስጠ ድርጅት አሠራሩ ምን ይመስል ይሁን?
ጆሮ ለባለቤቱ ባዳ ነው እንዲሉ በግንባር ቀደምትነት አገሪቷን እየመራ ያለው ደኢህዴን ይህንን ጉድ በጉያው ይዞ ወይ አለመንቃቱ ወይም ደግሞ አውቆ ዝም ማለቱ በራሱ አስገራሚ ነው፡፡ በደኢህዴን አመራር የደቡብ ኢትዮጵያ ልጆች በታሪክ ለመጀመሪያ ጊዜ በርካታ ቁልፍ የሀገሪቱን የፖለቲካ ሥልጣን ቦታዎች በብልሹ አሰራር ሳይሆን በብቃትና ችሎታቸው ይዘው አገሪቷን ወደላቀ የዕድገት መሥመር እየመሩ መገኘታቸው በግሌ ምን ያህል እንደሚያስደስተኝና እንደሚያኮራኝ ለመግለፅ ቃላት ያጥሩኛል፡፡ ታዲያ ምነው፤ “የራሷ አሮባት የሰው ታማስላለች“ እንዲሉ ደኢህዴን የብብቱን ሥር ጉድ እጉያው አስቀምጦ የሶማሊያን፤ የሱዳንን፤ የደቡብ ሱዳንንና የሌሎች አለማትን ጉዳዮች ለማቃናት ሲታትር ይታያል፡፡ ብራቮ ደኢህዴን! ነገር ግን ማስተካከልን ከቤትህ ጀምር እለዋለሁ፡፡ 
አለበለዚያ ምን ተብሎ ሊወሰድ ይችል ይሆን? ምናልባት አንድ ሐሜት የሰማሁት እውነት ሊሆን ነው ማለት ነው፡፡ “የደኢህዴን ባለስልጣናት ትኩረት ሰጥተው የሚያዩት እራሳቸው የመጡበትን አካባቢ ሕዝብ ጉዳይ ብቻ ነው፡፡ የራሳቸው ብሔር ችግር እስካልተፈጠረበት ድረስ መስሚያ ጆሮ የላቸውም፡፡ ቢሰሙም ችግሮች አድገው ጫፍ ከደረሱ በኋላ እንጂ ተገቢውን እርምጃ በወቅቱ በመውሰድ ችግሮች በእንጭጩ እንዲቀጩ የማድረግ አሰራርን አላጎለበቱም” ሲባል ሰምቻለሁ፡፡ ከዚህ አይነቱ ግዴለሽነት ደግሞ ይሰውረን እላለሁ፡፡ ይህ እውነት ከሆነማ በአሁኑ ሰዓት በትልቁ የደኢህዴን መዋቅር ደረጃ ጋሞን የሚወክል የጋሞ ተወላጅ ስለሌለ የጋሞ ሕዝብ “የተበደልኩ አቤቱታ“ ወቅታዊ ምላሽ የማግኘት ዕድሉ አጠራጣሪ ይሆናል ማለት ነው፡፡ •ረ የሰይጣን ጆሮ ይደፈን! በዚህ እንኳን አላምንም፡፡ ከደኢህዴን ግን መልስ እንጠብቅ! 
3. የዚህ ዓይነቱ የጥፋተኞች የመም አሠራር መንግሥታዊ የአቋም መግለጫ የሆነ ያክል እንዲህ እስኪገዝፍ ድረስ ኢህአዴግሥ እንደምን ዝም አለው? 
ይህ በራሱ ኢሕአዴግ ብቻ ሊመልሰው የሚችለው ጥያቄ ቢሆንም በቅርቡ የጋሞን ሕዝብ ወክለው የሕዝቡን “የተበደልኩኝ አቤቱታ“ ለተለያዩ የመንግስት መዋቅሮች ሲያቀርቡ የነበሩ ሽማግሌዎች ከአንዳንድ ታላላቅ ባለስልጣናት ጋር ባደረጓቸው ውይይቶች የተነሱ ሐሳቦች አመላካች የመልስ አቅጣጫዎችን ጠቁመዋል ሲባል ሰምቻለሁ፡፡ በጋሞ ሕዝብ ላይ ይደርሱ የነበሩት በደሎች እውነተኛ ገጽታቸው ለኢሕአዴግ እንዳይደርስ ሆን ተብሎ የሚሠራ የማሳሳቻ ወሬ ፍብረካ እንደነበረ መስማታቸውን ሽማግሌዎቹ ይናገራሉ፡፡ 
ከላይ በቁጥር 1 ላይ ያየነው የቃል ኪዳኑ አባላት ስብስብ ኢሕአዴግን እስከማሳሳት ድረስ ተጽዕኖ የመፍጠር አቅም ላይ መድረሱን ከዚሁ ማየት ይቻላል፡፡ በጋሞ አካባቢ በተደጋጋሚ ይደርሱ የነበሩ የአስተዳደር በደሎችን በመቃወም ሕዝቡ የሚያሰማው ድምፅም ቢሆን ለኢሕአዴግ የሚደርሰው በጋሞ ጎፋ እና በደቡብ ክልል ላይ በዞኑ ሕዝብ ስም የፖለቲካ ስልጣኑን ጠቅለው በያዙት የቃል ኪዳኑ አባላት በኩል ነበርና ሁሌም የሚባለው “ከሥልጣን የተባረሩ የጋሞ ልጆች የሚፈጥሩት ሁካታ ነው፤ የጥገኞች አጀንዳ ነው፤ የተቃዋሚ ድርጅት አባላት ሴራ ነው“ እና የመሳሰሉት ሰበቦች እየተሰጡት መቆየቱን መረዳት ተችሏል፡፡ በዚህም አሠራሩ ሕዝቡ የደረሱበት በርካታ በደሎች ትክክለኛ ገጽታቸውን ከኢሕአዴግ በመሸሸግ ሕዝቡን በአፈና ውስጥ ለማኖር ተችሎታል ማለት ነው የቃል ኪዳኑ አባላት ስብስብ፡፡ ሆኖም ኢሕአዴግ በመረጃ እና ደሕንነት ሥራው እጅግ የተዋጣለት ድርጅት እንደመሆኑ መጠን እነዚህን ጉዳዮች በሚገባቸው ደረጃ ባያውቅ እንኳን በመጠኑም ቢሆን ያጣቸዋል የሚል እምነት የለኝም፡፡
4. እነዚህ ጉዳዮች የሚፈፀሙበት ዞን እስከ ስሙ ጋሞ ጎፋ ሲሆን በዚህ ዞን ደረጃና በተለያዩ የሀገሪቱ የአስተዳደር እርከኖች ላይ እንደ ጎፋ ሕዝብ ሁሉ የጋሞም ሕዝብ ተወካዮች ይኖሩታል ብዬ አምናለሁ፤ ይህ ሕገ-መንግሥታዊ ነውና፡፡ ታዲያ እነዚህ ተወካዮች አሁን እየተነሱ ያሉትን በጋሞ ብሔር ላይ የሚፈፀሙ የመብትና የጥቅም በደሎች እንደምን ቢያይዋቸው ነው በደሎቹ ያለ ተቃውሞ ድምፅ ይህን ያህል የገዘፉት? 
ይህ ጥያቄ ሊመለስ የሚችለው በየመዋቅሩ ደረጃ ባሉ የጋሞ ሕዝብ ተወካይ እንደራሴዎችና ባለሥልጣናት ብቻ ይሆናል፤ የጥያቄው ውስጠት እራሱ የሚያነጣጥረው በተወካዮቹ የግልና የወል አስተዋፅኦ ላይ በመሆኑ፡፡ ሌሎችም ለጉዳዩ ቅርበት ያላችሁ አንባቢያን መልስ ካላችሁ ብታስነብቡን ወይም ብታስደምጡን ደስተኛ ነኝ፡፡
እንግዲህ የማዶላ ቡቱቶ ፅሑፍ እና ፅሑፉ ያመጣቸው መዘዞች ሰንኮፋቸው ያለው ከጽሑፉ ውስጥ ሳይሆን በጎፋ ዞን ጥያቄ ዙሪያ በሚሠራው የዞን ጥያቄው ቃል ኪዳን አባላት ስብስብ ዘንድ እንደሆነና ይህ ስብስብ ይህን ዓላማውን ለማሳካት ሲል የሚያደርሳቸውን ሕዝባዊ በደሎች በትንታኔ ለመጠቆም ሞክርያለሁ፡፡ ከዚህ ቀጥሎ ደግሞ የነማዶላ መዘዝ አሁን የደረሰበትን ደረጃ እንመለከት ዘንድ ጋብዣችኋለሁ፡፡

የማዶላ የሕትመት ዝግጅት፤የጽሑፉ ሥርጭትና የጋሞ ሕዝብ የተቃውሞ እንቅስቃሴ
ማዶላ የተሰኘው ቡቱቶ ጽሑፍ ከመታተሙ በፊት የስብስቡን የደኢህዴን ጽ/ቤት ቁንጮ ጨምሮ የጎፋ ዞን ጥያቄው ቃል ኪዳን አባላት ሶፍት ኮፒው ተልኮላቸው የአርትኦት ሥራ እንደሰሩለትና በጨረሻም ሕትመቱን እንዳፀደቁለት ውስጥ አዋቂ ምንጮች አረጋግጠዋል፡፡ በተጨማሪም ከነዚህ አባላት መካከል አቶ ዳዊት ፋንታዬን ጨምሮ የሕዝብ ጥያቄ ያስጨነቃቸው አንዳንድ ባለስልጣናት ሶፍት ኮፒውን መቀበላቸውን በተደጋጋሚ መድረኮች ላይ በራሳቸው አንደበት አምነዋል፡፡ ይህና አሁን በፖሊስ በኩል እየተገኙ ያሉ የሕትመቱ የፋይናንስ ድጋፍ መረጃዎች ከላይ ላስቀመጥኩት የነማዶላ አስተሳሰብ ሰንኮፍ ትክክለኛ አድራሻ ትንታኔ ተጨማሪ ማስረጃዎች ይሆናሉ፡፡ 
ይህ ነው መሰል ሕዝቡንም የጽሑፉ አዘጋጅ ተብዬ ታደለ ቱፋን ብቻ ሳይሆን ከበስተጀርባው የተሰለፉትን ረጃጅም እጆች ፍለጋ ላይ እንዲጠመድ ያደረገው፡፡ ጽሑፉ ታትሞ ለአንባቢያን እጅ ከደረሰ ወዲህ የጽሑፉ ነውረኛ ክፍሎች የተመለከቱ አንባቢያን በቁጭት ተነሳስተው ጉዳዩን ለመላው ሕዝብ አዳርሰዋል፡፡ ሕዝቡም በዚህ ጽሑፍ እጃቸውን ያስገቡ ሐይሎች የመጨረሻ የዝቅጠት ጣራ የሆነውን የዕብሪተኝነት ስድብ አንብቦ ካየው በኋላ ቁጣውን በአካባቢው መንግሥት አካላት ላይ ገልጽዋል፡፡ 
እንደ ውስጥ አዋቂ ምንጮች አባባል የሕዝቡን ቁጣ የተመለከቱት የቃል ኪዳኑ አባላት የቡቱቶ ጽሑፍ አዘጋጅ ተባባሪያቸው የሆነውን ግለሰብ ከአዲስ አበባ ወደ አርባ ምንጭ በመጥራት የማሰርና ከዚያም እራሳቸው የዋስትና ገንዘብ አቅራቢ፤ አስፈቺ እና በመንግስት ለስራ በተሰጣቸው መኪና ሸኚ ሆነው ግለሰቡን ወደ ቤቱ በመሸኘት በሕዝብ ላይ የመቀለድ የቆየ ልምዳቸውን ደግመው አሳይተዋል፡፡ ሆኖም በደሉ እጅግ የበዛበትና ብሎ ብሎም ስድቡ ወደ ሕትመት ደረጃ የደረሰበት የጋሞ ሕዝብ “የተበደልኩ“ አቤቱታውን ለዞኑ አስተዳደር በማቅረብና አስተዳደሩን በማስጨነቁ ምክንያት (በኋላ የካደው ቢሆንም) አስተዳደሩ የጋሞ ሕዝብ አርባ ምንጭ ላይ አቤቱታውን በሰላማዊ ሰልፍ እንዲገልጽ ፈቃድ ሰጥቶ ነበር፡፡ ይሁን አንጂ የሰላማዊ ሰልፉ ቀን በደረሰ ጊዜ የተፈቀደለትን አቤቱታ የማቅረብ ሰላማዊ ሰልፍ ለማድረግ የወጣውን ሕዝብ አስተዳደሩ በፌዴራል ልዩ ሐይል በማስደብደብና በማሳሰር በሕዝቡ ላይ ተጨማሪ ውርደትን አስከትሏል፡፡
ይህም ቢሆን ሕዝቡ ትግሉን አጠናክሮ በመቀጠል ይህ ጉዳይ ለተለያዩ የወረዳ፤የዞን፤የክልልና የፌደራል አካላት ጆሮ አንዲደርስና ፍትሐዊ ምላሽ እንዲሰጠው የመጠየቁን ሒደት ቀጥሎበታል፡፡ በዚህ መካከል ሕዝቡን በአፈና ሥር ይዞት የቆየው የቃል ኪዳኑ ስብስብ የህዝቡን ጥያቄ ለማኮላሸት ሌት ተቀን መዳከሩም አልቀረም፡፡ አንዴ የወረዳ አመራሩን ሌላ ጊዜ ደግሞ ሕዝቡን በተለያዩ ቡድኖች አከፋፍሎ በመጥራት ማስፈራራቱን ቀጥሏል፡፡ 
መቼም ጆሮ የማይሰማው የለ አሁን አሁን ደግሞ የቃል ኪዳኑ አባላት የተለያዩ የሕዝብ ማጭበርበሪያ ድራማዎችን እየተወኑ አንደሚገኙ ይወራል፡፡ ሕዝቡ “ተበደልኩ፤ የበደሌም አድራጊዎች እናንተ ናችሁ!“ ብሎ አቤቱታ ሊያቀርብ ያሰበበትን ሰላማዊ ሰልፍ ነጥቀውት “ሰልፉንም እኛ ነን የምናዘጋጅላችሁ፤ የጥያቄያችሁን መፈክርም እኛ ነን የምንጽፍላችሁ፤ ሰልፉን የሚወጡ ሰዎችንም ዝርዝር እኛ ነን የምንወስንላችሁ” በማለት ከሕዝብ ጋር ተፋጠው እንደሚገኙ ይነገራል፡፡ ልብ አድርጉ እንግዲህ! የአካባቢው መንግሥት የራሱ ሰዎች በሚሳተፉበት ሰላማዊ ሰልፍ ላይ ለራሱ በራሱ ጥያቄዎችን በመፈክር መልክ አቅርቦ ራሱም መልስ ሰጪ የሚሆንበትን ሰላማዊ ሰልፍ ልናይ ነው! 
ይህ ሲገርመን ሌላ አስደናቂ ዜና ተሰማ፡- የጋሞ ጎፋ ዞን አመራር የሆኑ የቃል ኪዳኑ አባላት በማዶላ መዘዞች ዙሪያ ፖለቲካዊ ግምገማ ለማካሔድ ወደ ክልሉ መዲና ሐዋሳ ዘልቀዋል፤ የሚል፡፡ መዝለቁስ ባልከፋ፤ ነገሩ ሌላ ማጭበርበሪያ ድራማ መሆኑ ነው እንጂ፡፡ መቼም እነዚህ የቃል ኪዳኑ አባላት የፖለቲካ ድራማ ብቃታቸው ምን ያህል ከፍተኛ እንደሆነ ታዘቡልኝ፡፡ ግምገማው የተደረገው በሐዋሳ ሆነ እንጂ ገምጋሚዎቹም ተገምጋሚዎቹም ራሳቸው ከአርባ ምንጭ ወደ ሐዋሳ የዘለቁት የአመራር አባላት ብቻ መሆናቸው የድራማውን ኪነጥበባዊ ጥልቀትና ምጥቀት ክፍ ያደርገዋል፡፡ 
ይህንን በዊኪሊክስ ሰምቶ የነገረኝን አንዱ ወዳጄን “እነዚህ ሰዎች እርስበራሳቸው ለመገማገም እስከ ሐዋሳ የሚያስመጣቸው ምን የተለየ ምስጢር ይኖር ይሆን?“ ብዬ ስጠይቀው “ምናልባት የሐዋሳን ከተማ ኮንፍራንስ ቱሪዝም ለማሳደግ ካላቸው ዕኑ ፍላጎት በመነሳት ያልተወራረደ የመንግሥት በጀት ኖሯቸው ያንኑ ለማወራረድ ፈልገው ቢሆንስ “ ብሎ ፈገግ አሰኝቶኛል፡፡ እንደዚሁም ከሚከሳቸው ሕዝብ ፊት ገለል ብለው በመመለስ ክልካዊ ግምገማ አድርገው እንዳለፉ ለማስመሰል ሳይሆን አይቀርም የሚሉም ለነገሩ አልታጡም፡፡ ክልል ደርሶ የአለቃቸውን ቡራኬ ተቀብለው መመለሱ ሐጢያታቸውን የሚያስተሰረይላቸው አይመስለኝም፡፡ “በሩን የቀረቀረ ሳይሆን ሐጢያቱን የተናዘዘ ብቻ ይተርፋል“ አሉ ጋሞዎች ሲተርቱ፡፡
እንግዲህ በነማዶላ መዘዝ የተለኮሰባቸው እሳት መቆሚያ መቀመጫ ያሳጣቸው የቃል ኪዳኑ አባላት የሚይዙ የሚጨብጡትን አጥተው እየተቅበዘበዙ ይገኛሉ፡፡ የሐጢያታቸው እሳት በልቶ አመዳቸው እስኪቀር ድረስ የሚርያፉም አይምሰላችሁ፡፡ ጣር እንደያዘው የሞት ታጋይ ያገኙትን ሁሉ መቦጫጨራቸው አይቀርም፡፡ ከተሳካላቸውም አሁን የያዙትን የሕዝብ ሥልጣን ተጠቅመው ሐጢያታቸውን ወደ ንጹሐን በማሻገር እነሱ ደግሞ በአዲሱ የስልጣን ክፍፍል ከተጠያቂነት የሚያስመልጧቸውን ቦታዎች ለመያዝ በሳምንት ሰባት ቀናት፤ በቀን 24 ሰዓታት መስራታቸው የሚቀጥል እንደሆነ ይሰማኛል፡፡
የጋሞ ሕዝብ ቀጣይ የመልስ ፍለጋ ጉዞ
እንደ አንድ የጋሞ ብሔር አባል ማለትም እንደ ጉዳዩ ባለቤት እና እንደ ሰሞኑ ሁኔታዎች ተከታታይ እንደዚሁም እንደ ኢ-ፍትሐዊነት ተቃዋሚ፤ ሕዝቡ በቀጣይ ጊዜያት መከተል ይገባዋል ብዬ የማምንበትን የፍትሕ ጥያቄ መንገድ ቀጥሎ ባሰፈርኩት አስተያየቴ አቀርባለሁ፡፡
የሕዝቡ የእስካሁኑ የጥያቄ አቀራረብ ጉዞ በሰላማዊነቱ እና ዲሞክራሲያዊነቱ እንከን የማይወጣለት መሆኑን ተገንዝብያለሁ፡፡ የዞኑ አስተዳደር ለፌደራል ፖሊስ ስለሕዝቡ የተሳሳተ መረጃ እስከመስጠት ደርሶ ሕዝቡን በልዩ ሐይል ያስደበደበ እና ያሳሰረ ቢሆንም ሕዝቡ የጥያቄውን ትክክለኛነት ለፖሊሱ የበላይ አካላት አስረድቶ የአስተዳደሩን ስህተት በማጋለጥ የታሠሩ ልጆቹን ከአንድ ቀን ባልበለጠ ጊዜ ውስጥ አስፈትቷቸዋል፡፡ አንድ ቀንም ቢሆን መታሠራቸው ተገቢነት አለው የሚል መከራከሪያ እንደሌለኝ አስምሩልኝ፡፡ ጨዋው፤ ሰርቶ ከማደር እና አካባቢውን ለማልማት ከመትጋት ሌላ አጀንዳ የሌለው የጋሞ ሕዝብ አሁንም ቢሆን ኢ-ፍትሐዊነትን የመቃወም ጥያቄውን ማቅረብ ያለበት ጨዋነቱን ጠብቆ ማንኛውንም የሌላ ብሔር ብቻ ሳይሆን የብሔር አባላትንም ቢሆን መብታቸውን በማይነካ ሁኔታ በሰለጠነ አግባብ ብቻ መሆን ይገባዋል፡፡ ከብሔርና ከብሔር አባላት ጋር አንዳችም ችግር የለበትምና፡፡ ጥያቄው ማተኮር ያለበት የግፍ አገዛዝ ባሰፈኑበት ሴረኛ ባለስልጣናትና እነሱ በፈጠሩት የክፉ አሠራር ሰንሰለት በተሳተፉ ግለሰቦች ዙሪያ ሊሆን ይገባዋል፡፡ 
ይህንን ከመተግበር አንፃር እስካሁን ሕዝቡ በተወካዮቹ በኩል እንዲሁም በወረዳዎች እና በአርባ ምንጭ ከተማ አስተዳደር ደረጃ ድምፁን ከፍ አድርጎ ማሰማት ችሏል፡፡ ተወካይ የሀገር ሽማግሌዎች በየእርከኑ ለሚገኙ የመንግስት አካላት ባቀረቧቸው ማመልከቻዎች የማዶላ ጽሑፍ አዘጋጁ አቶ ታደለ ቱፋ ለሕግ እንዲቀርብ፤ ማዶላ የተሰኘው የጽሑፍ ቡቱቶዎች ጥራዝ ከያለበት ተሰብስቦ በሕዝብ ፊት በዞኑ ዋና ከተማ ውስጥ ጋሞ አደባባይ ላይ እንዲቃጠል፤ ይህ ጽሑፍ በምንም መልኩ ለማጣቀሻነት እንዳይውል በሕግ እንዲታገድ፤ ከማዶላ ጽሑፍ ጀርባ በምንም መልኩ እጃቸው ያለበት አካላትና ግለሰቦች በአስቸኳይ ተጣርተው ለሕግ እንዲቀርቡ እና የጋሞ ሕዝብ በማዶላ ጽሑፍና ተመሳሳይ የክፋት ድርጊቶች የደረሰበትን በደል በሰላማዊ ሰልፍ እንዲገልጽ እንዲፈቀድለት ጠይቀዋል፡፡ ለያንዳንዱ ጥያቄ ተግባራዊ ምላሽም እየተጠበቀ ይገኛል፡፡
በሌላ በኩል የጋሞ ሕዝብ በየወረዳ ከተማው እና ከተማ አስተዳደር መዋቅሮች በአስር ሺዎች በሚቆጠር የሕዝብ ብዛት ሰላማዊ ሰልፍ እየወጣ ቁጣውን እየገለፀ እና ጥያቄውን ለመንግስት እያቀረበ ይገኛል፡፡ በዚህ ሒደት ውስጥ እስካሁን የዲታ ወረዳ፤ የዳራ ማሎ ወረዳ፤ የጨንቻ ወረዳ እና የአርባ ምንጭ ከተማ ነዋሪ ሕዝቦች በየከተማቸው በሚያስደነግጥ የህዝብ ቁጥር እየወጡ ድምፃቸውን ከማሰማታቸውም በላይ በሕዝብ መብት፤ ክብርና ጥቅም ላይ የጥፋት ሴራ የዘረጉ ባለስልጣናት ያሏቸውን በስም እየጠሩ ከአሁን በኋላ እነዚህ ግለሰቦችና ተላላኪዎቻቸው ሊመሩዋቸው እንደማይችሉና በአስቸኳይ ከስልጣናቸው ወርደው ለፍርድ እንዲቀርቡ ጠይቀዋል፡፡ ይህ ሒደት በሌሎችም ወረዳዎች በቀጣይ እንደሚከናወንና የቀሪ ወረዳዎች ሕዝቦችም ተመሣሣይ ዝግጅት እያደረጉ እንደሚገኙ ይነገራል፡፡ ተመሣሣይ በሰላማዊ ሰልፍ የሕዝቡን ድምፅ የማሰማት ተግባር በአዲስ አበባ ነዋሪ የጋሞ ብሔር አባላትም በቅርቡ እንደሚፈፀም አንዳንድ የወሬ ምንጮች ይጠቁማሉ፡፡
ይህ ሁሉ የህዝቡ ጥያቄ ትክክለኛ መስመሩን ይዞ እየተጓዘ ስለመሆኑ ጉልህ ማሳያ ነው፡፡ ይሁን እንጂ አሁን በማስ እየቀረበ ካለው የፍትሕ ጥያቄ በኋላ ሊኖሩ የሚገባቸው የጥያቄ አቀራረብ ሥርዓቶች መልክ ያለውን አሠራር የተከተሉ መሆን አለባቸው ባይ ነኝ፡፡ እንዴት ብትሉኝ፡- በሕዝቡ በኩል አሁን እየቀረቡ ያሉት ጥያቄዎች ተንጠባጥበው ሳይቀሩ ተለቅመው በየመልካቸው ማስኬድ በሚችሉ የሕዝብ ተወካዮች በኩል ሊቀጥሉ ይገባል፡፡ ለምሣሌ አሁን እየቀረቡ ያሉት የሕዝቡ ጥያቄዎች በሦስት ፈርጅ ሊከፈሉ ይችላሉ፡- ሕጋዊ፤ አስተዳደራዊና ፖለቲካዊ፡፡ ታዲያ እነዚህ ጥያቄዎች የየራሳቸው አቅራቢ ባለቤት ተፈጥሮላቸው ካልተንቀሳቀሱ የሕዝቡ ጥያቄዎች ሊንጠባጠቡ እንደሚችሉ ስጋት አለኝ፡፡
በመሆኑም የነታደለ ቱፋን፤ የጽሁፋቸውን፤ እንዲሁም የመካሪ ዘካሪ እና ተባባሪዎቻቸውን ሕጋዊ ጉዳዮች የሚከታተል ጉዳዩ የሚመለከታቸው የጋሞ ብሔር ተወላጅ ከመሆንም አልፎ ለሕዝቡ ታማኝ የሆኑ የሕግ ባለሙያዎች ቡድን ሊወከል ይገባል፡፡ ይህንን የምልበት ዋናው ምክንያት በአሁኑ ሰዓት በጋሞ ጎፋ ዞን የፍትሕና ዳኝነት መዋቅር ላይ የሚገኙ ባለሙያዎችም ቢሆን የፖለቲካ ጡንቻውን እጅግ አፈርጥሞ ፈላጭ ቆራጭ ከሆነው የቃል ኪዳኑ አባላት ስብስብ የተፅእኖ ክልል ውጪ ሊሆኑ ስለማይችሉ ይህንን ተፅዕኖ በሕዝብ ወገንተኝነት ሊቋቋም የሚችል ነፃና ሕዝባዊ የህግ ባለሙያዎች ቡድን ስለሚያስፈልግ ነው፡፡ እንዲህ አይነቱ ቡድን የሕዝብ አደራ ከተሰጠው ሊደርሱበት የሚችሉ ተፅዕኖዎችን ሁሉ ተቋቁሞ በማለፍና እስከ መጨረሻው ጫፍ በመጓዝ ሕግና ፍትሕ እንዲያሸንፍ የማድረግ አቅም ይኖረዋልና፡፡
በተጨማሪም በየማህበራዊ ሚዲያው እንደምናነበውና ከውስጥ አዋቂ ምንጮች እንደሚሰማው የቃል ኪዳኑ አባላት ቡድን በዞኑ ውስጥ ያለውን የፖሊቲካ ሥልጣን ጠቅልሎ በመያዝና ለየት ያለ ሐሳብ ይዞ የቀረበን አመራር ሁሉ በማስወገድ እራሱና የራሱ ተላላኪዎች ብቻ የሚቆጣተሩትን መዋቅር መፍጠር በመቻሉ ያለ አንዳች የመረጃ መሹለኪያ ቀዳዳ እራሱን በስልጣን አደላድሎ እጅግ የከፋ የሙስናና በስልጣን የመባለግ ተግባር ላይ በመሰማራት ለሕዝብ ልማትና መልካም አስተዳደር የሚመደበውን የዞኑን በጀትና ልዩልዩ ገቢዎች ወደየግል ኪሱ ሲያጋብስና ይህንኑ የመቀራመት ሥራ ላይ ተጠምዶ መቆየቱም ይነገራል፡፡ ይህን ዓይነቱን አስፈሪና አደገኛ ጉዳይ አደራጅቶ ለሕግ ለማቅረብና የህዝብ ገንዘብ ለሕዝብ እንዲመለስ ለማድረግም ጭምር ከላይ ያልኩት አይነት የህግ ባለሙያዎች ቡድን ያስፈልጋል ባይ ነኝ፡፡
አስተዳደራዊና ፖለቲካዊ እርምጃዎችን እንደ መልስ በሚፈልጓቸው ጥያቄዎች ዙሪያ ደግሞ ተገቢና ፍትሐዊ መልስ እስኪገኝ ድረስ ጉዳዩን የሚከታተሉ እስከ ዛሬ ድረስ የመሩትን አይነት ጠንካራ የሐገር ሽማግሌዎች ከአርሶ አደሩ፤ ከምሁሩ፤ ከነጋዴውና ሠራተኛው ተመርጠው የሕዝብን አደራ መረከብ አለባቸው፡፡ እነዚህ ሽማግሌዎች እስካሁን ድረስ ለመንግስት የቀረቡትን ጥያቄዎች ምላሽ በመሻት በየወቅቱ ለሕዝቡ የግብረ መልስ መረጃ ማቀበል አንዱ ሕዝባዊ ሐላፊነታቸው ሊሆን ይገባል፡፡ ከዚህም በተጨማሪ ለመንግሥት የሚቀርቡ ማብራሪያዎች፤ ማስረጃዎችና ተጨማሪ መረጃዎች ሲኖሩ ይህንን የማከናወን ሐላፊነትም የነዚህ ሽማግሌዎች ይሆናል፡፡
ንፁሕ ፖለቲካዊ እርምጃዎችን እንደ ምላሽ ለሚፈልጉ ጥያቄዎች ደግሞ ንፁሐንና አብዮታውያን የፌደራል፤ የክልል፤ የዞንና የወረዳ አመራሮች ሚናቸውን ሊጫወቱ ይገባል፡፡ በዞናችን ተንሠራፍቶ የቆየውን አይነት ስሙ አብዝቶ የጎደፈ እና ሕዝብ የጠላውን የፖለቲካ አሠላለፍ ማስቀጠሉ ከአሁን በኋላ የሚቻል አይሆንም፡፡ በአንፃሩ ደግሞ የሕዝቡ ፍትሐዊ ጥያቄ ከአብዮታውያን የፖለቲካ አመራሮች ትግል ጋር ሲደጋገፍ የእንዲህ አይነቱን ብልሹ አሰራርና አመራር ግብዓተ መሬት ማፋጠኑ ሳይታለም የተፈታ ነው፡፡ በመሆኑም መላው ሕዝብ፤ የሕግ ባለሙያዎች፤ የሕዝብ ተወካይ ሽማግሌዎችና የፖለቲካ አመራሩ ለሕግ፤ ለፍትሕና ለዲሞክራሲ በመቆም በሕዝብ ጫንቃ ላይ ተንደላቆ እየኖረ የሕዝብን በደሎች ሲያባዛ የነበረውን የፖለቲካ አሰላለፍ ከስሩ አፈራርሶ እንደሚጥለውና በጋሞ ጎፋ ዞን ማህበራዊ ፍትሕን እንደሚያነግሥ አንዳች ጥርጥር የለኝም፡፡
ይህ ሁሉ ሆኖም ቢሆን ሥር-ነቀል ለውጥ ባይመጣስ? 
የዚህ ዓይነቱ ጥያቄ የጨለምተኝነት አስተሳሰብ ውጤት የሚመስል ቢሆንም መቼም ለምን ተነሳ አይባልም፤ በቀቢጽ ደረጃም ቢሆን የመሆን ዕድል ሊኖረው ይችላልና፡፡ ታዲያ ይህ ሁሉ ሆኖም ለውጥ ካልመጣ መፍትሔው ትግሉን አሁንም በሰላማዊና ዲሞክራሲያዊ መንገድ ማስቀጠል ይሆናል፡፡ በዚህ ጊዜ ግን የትግል ስልቱ ሊቀየር ይገባል የሚል ዕምነት አለኝ፡፡ ምን ዓይነት ብትሉኝ ወቅታዊ ሁኔታዎችን ያማከለ አስተያየቴን በቀጣዩ ጽሑፌ ይዤላችሁ እቀርባለሁ፡፡ እስከዚያው ብዙ የማህበራዊ ድረ-ገጽ ተጠቃሚዎች እንደኔው በአዲስ መልክ የሚገቡና ነባሮችም ጭምር ብዙ ሐሳቦቻቸውን እንደሚያካፍሉኝ ተስፋ አደርጋለሁ፡፡
ቸር እንሰንብት!!
ጋሞና ገራ

     Give your opinion.

Assres Kidane Kassa (Assres Kenito Kalsa) 2016-08-04

ሲጀመር ዋና ከተማ አዋሳ የሆነው? ከጥንት ጀምሮ አርባምንጭ ነበረ። እንዴት ፅሁፉ ከመታተሙ በፊት ሳንሱር (censure) አልተደረገም? በኢትዮጵያነቴ ከመኩራቴ ባሻገር በጋሞነቴ በጣም እኮራለሁ፣ አቅራራለሁ። በቅርቡ ይሄ ታደለ ቱፋ በተባሉ ግለሰብ ተደርሶ በቲኤስ ማተሚያ ቤት ታትሞ ለንባብ የበቃው “ማዶላ ማላና ዶጋላ” የተባለ ዝባዝንኬ ፅሁፍ በጣም አዝኛለሁ። አባቴ አለቃ ከንቶ ካልሳ (ነፍሱን ይማረዉና) በሕይወቱ ቢኖር ምን ያህል ይበሳጭ እንደነበረ መገመት አያዳግትም። ከጋሞ ብሄረሰብ ምሁራን ጎን ነኝ። ዲያስፖራ ያለን የጋሞ ምሁራን የምንችለው ነገር ካለ ለመተባበር ዝግጁ ነን። assres@gmail.com